
የመጀመሪያዋ የሴት ዲፕሎማት!
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዚህ ሳምንት የካቲት 05/1948 የመጀመሪያዋ ሴት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል እና ምክትል ሊቀ መንበር በመኾን እስከ 1952 ዓ.ም ድረስ ያገለገሉትን የክብር ዶክተር ስንዱ ገብሩን እንቃኛለን።
ስንዱ ገብሩ በጥር 06/1908 ዓ.ም በሸዋ ክፍለ ሀገር፣ በአዲስ ዓለም ከተማ ነው የተወለዱት። አባታቸው ታዋቂው ዲፕሎማት ከንቲባ ገብሩ ናቸው። የመጀመሪያ ትምህርታቸውን በቤታቸው ካገኙ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል። ቀጥለውም ትምህርታቸውን በስዊስ እና በፈረንሳይ በመዘዋወር በዲፕሎማ አጠናቅቀዋል።
በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ወይዘሮ ስንዱ ከአርበኞች ጋር በመቀላቀል በጀግንነት ተዋግተዋል። በዚህ ወቅት ቀይ መስቀልን በማቋቋም ለተጎዱ አርበኞች እርዳታ አድርገዋል።
በፋሺስቶች እጅ ከወደቁ በኋላ በጣሊያን እስር ቤት ለዘጠኝ ወራት ያህል ታስረዋል። ከእስር ከተፈቱ በኋላም ለአርበኞች የሥነ ልቦና ድጋፍ በመስጠትና መረጃዎችን በማቀበል ትግላቸውን ቀጥለዋል።
ከድል በኋላ ወይዘሮ ስንዱ ለሁለት ዓመታት በደሴ ከተማ በሚገኘው የወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ በመኾን አገልግለዋል። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ መምህር ኾነዋል።
በትምህርት ቤት ቆይታቸውም “ኮከብ ያለው ያበራል ገና”፣ “የየካቲት ቀኖች” እና “የኑሮ ስህተት” የሚሉ ተውኔቶችን ደርሰዋል።
ከ1948 እስከ 1952 ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያዋ ሴት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልና ምክትል ሊቀ መንበር በመኾን ሠርተዋል። በዚህ ቆይታቸውም የሴቶችን ሰብዓዊ መብት እና እኩልነት ለማስከበር ጠንክረው ሰርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ፕሬዝዳንት በመኾን እና በምዕራብ ጀርመን የትምህርት አታሼ በመኾን አገልግለዋል።
ለሀገራቸው ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥት ሳባ የወርቅ ኒሻን፣ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሸልመዋል።
የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ አባል፣ የሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ጀግና አርበኛ፣ ፀሐፊ ተውኔትና ደራሲ የክብር ዶክተር ስንዱ ገብሩ በ2001 ዓ.ም በ93 ዓመታቸው አርፈዋል።
ኢትዮ ሪፈረንስ የተሰኘ ድረገጽን በመረጃ ምንጭነት ተጠቀምን።
ሀገሩን ያኮራው አርበኛ !
ሌተና ጀነራል ጃገማ ኬሎ፣ በቅፅል ስማቸው የበጋው መብረቅ በመባል የሚታወቁት ጀግና የኢትዮጵያ አርበኛ ናቸው። የተወለዱት በ1913 ዓ.ም ሲኾን፣ በ15 ዓመታቸው ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት አርበኞችን ተቀላቅለው ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ የጦር መሪና አሥተባባሪ በመኾን የኢጣሊያን ጦር በተለያዩ ቦታዎች ድል በማድረግ ይታወቃሉ። በተለይም የአዲስ ዓለም ምሽግን የሰበረው በእርሳቸው መሪነት የነበረው ጦር ነው።
ከአምስት ዓመታት የነፃነት ትግል በኋላ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ሲባረር በአካባቢያቸው አሥተዳደር ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው። በ1934 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የሻለቃነት ማዕረግን ተቀብለዋል።
በወታደራዊ ሕይወታቸውም በተለያዩ የከፍተኛ መሪነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን የብርጌድ፣ የክፍለ ጦር እና የብሔራዊ ጦር አዛዥ በመኾን የሌተናል ጄኔራልነት ማዕረግ ደርሰዋል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሚገኙ የጦር አካዳሚዎች የትምህርት እድሎችን አግኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በባሌና በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛቶች ጠቅላይ ገዢ በመኾን ለሕዝባቸው አገልግለዋል።
ጡረታ ከወጡ በኋላም ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም በጽናት የሠሩ ሲኾን፣ ለሀገራቸው ላበረከቱት ልዩ አስተዋጽኦ አጼ ኃይለ ሥላሴን ጨምሮ በርካታ ሀገሮችና ድርጅቶች የክብር ሽልማቶችን ሰጥተዋቸዋል።
ጀኔራል ጃገማ ኬሎ በተወለዱ በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት መጋቢት 29/2009 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር።
ኢትዮጵያን ፓትሪዎት ዶት ኦርግ የተሰኘ ድረገጽን በመረጃ ምንጭነት ተጠቀምን።
የዓለም የጤና ድርጅት ምሥረታ!
መጋቢት 29/1948 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት የተመሠረተበት ሳምንት ነው። ይህ ቀን በየዓመቱ የዓለም ጤና ቀን ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል። የዚህ ድርጅት መፈጠር ሀሳብ የመነጨው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ነበር።
በተለይም ብራዚል እና ቻይና ዓለም አቀፍ የጤና ጉዳዮችን በጋራ የሚከታተል አንድ ድርጅት መቋቋም አለበት የሚል ሀሳብ በጋራ አቀረቡ።
በዚህም መሠረት የዓለም የጤና ድርጅትን በ1946 በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የጤና ጉባኤ ላይ ፀደቀ። ይህ ድርጅት በቂ በኾኑ ተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት ከፀደቀ በኋላ በመጨረሻም በዚህ ሳምንት 1948 ዓ.ም በይፋ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል።
የዓለም የጤና ድርጅት መቋቋም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሀገራት የሕዝባቸውን ጤና ለማሻሻል በጋራ መሥራት አስፈላጊ እንደኾነ ያላቸውን እምነት አሳይቷል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዓለም የጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕዝብ ጤና ጉዳዮችን በመምራት ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ከአባል ሀገራት እንዲኹም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የጤና ችግሮችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲኹም የሰዎችን የጤና ኹኔታ ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ድርጅትም ነው።
ለመረጃ ምንጭነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረገጽን ተጠቅመናል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
