ቆም ብለን እናስብ!

42

ቆም ብለን እናስብ!

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2017 ዓ.ም(አሚኮ) ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም ማንኛውም ሰው የመማር መብት እንዳለው ደንግጓል፡፡ ሀገራት በተለይም ሕጻናትን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገብተው ማስተማር ግዴታቸው እንጅ ውዴታቸው አለመኾኑን አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም ትምህርት የሰው ልጆች የተሟላ ስብዕና ዕድገት መገንቢያ በመኾኑ ትምህርትን ማቋረጥ ወንጀልም ነው ብሏል።

የሰብዓዊ መብቶች እና መሠረታዊ ነጻነቶች መከበር የሚችሉት ትውልዱ በትምህርት ታንጾ ሲያድግ ብቻም ነው ይላል።

ስለኾነም ማንም አካል በምንም ምክንያት ትምህርትን ማቋረጥ፣ ትምህርት ቤቶችን መዝጋት ወይም ዜጎችን እንዳይማሩ ማድረግ የለበትም የተቋሙ የውሳኔ ማደማደሚያ ሀሳቡ ነው።

ካሰፈረው ድንጋጌ የምንረዳው ትምህርት በሁሉም ሀገራት ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ተጽዕኖ ነጻ መኾኑን ነው። ትምህርት ቤቶች በፖለቲካዊ ተቃርኖ እና አመክንዮ መቋረጥ እንደሌለባቸውም ያስገነዘበ ነው፡፡

በዓለም የፖለቲካ ታሪክ ሀገራት በውስጥ ፖለቲካቸው እሰጥ እገባ ውስጥ ሲገቡ ትምህርትን በአላማ እንዲቋረጥ ያደረጉበት የታሪክ አጋጣሚ የለም።

ዜጎች በመማራቸው የሚጠቅሙት የኾነን ቡድን ወይም መሪ ሳይኾን ሀገር እና ሕዝብን ነውና።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም”ማንኛውም ሰው የመማር መብት አለው” ቢልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጸመው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው ማለት እችላለሁ። ክልሉ የገጠመውን የሰላም እጦትን ተከትሎ ተተኪ ሕጻናት የመማር መብታቸውን ተነፍገዋል።

መምህራን ነጭ ጋዎን ለብሰው እና ጠመኔ ጨብጠው ሕጻናትን ዕውቀት በመገቡ ታግተዋል፤ ተገድለዋል፤ ተደፍረዋል፤ ተገርፈዋል።

“ነገር በምሳሌ፤ ጠጅ በብርሌ.” ያምራል እንዲሉ አበው ሀሳቤን ውኃ ቢሚያነሳ እና ሚዛን በሚደፋ ማስረጅ ላስደግፈው።

የአማራ ክልል በገጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት በ2017 የትምህርት ዘመን 3ሺህ 736 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ መዘጋት ብቻ ሳይኾን ጉዳትም ደርሶባቸዋል።

በትምህርት ዘመኑ ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ከነበረባቸው ከ7 ሚሊዮን 800 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ከ4 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ ተማሪዎች ያውም ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፤ ያሳዝናል!
ከ30 ሺህ በላይ መምህራን እና የትምህርት ቤት መሪዎች ወደ ሥራ ገበታቸው አልተመለሱም፡፡

መማር ከሚገባቸው ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙት ተማሪዎች 40 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ በማንም ይሁን በምንም ምክንያት ኢትዮጵያውያን ነን በሚሉ አካላት ትምህርት በመቋረጡ የ60 በመቶ ተማሪዎች መጻኢ ሕይዎት እየጨለመ ነው።

በተለይ ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ በመኾናችው ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና ደርሶባቸዋል፡፡
የደብተር ቦርሳ በትከሻቸው መያዝ ሲሹ ያለ ዕድሜያቸው ተድረው ልጅ አዝለዋል፡፡

እዚህ ላይ አንዲት የሰሜን ጎጃም አካባቢ ተማሪ ያለችውን ነባራዊ ሐቅ ለአስረጅነት ላንሳ፤ “ዓላማዬ ሳይንቲስት መኾን ነበር፤ ነግር ግን “ግጭት አፈር ይብላ! ከዓላማዬ አደናቀፈኝ፤ ሳልፈልግ በተጽዕኖ የልጅ እናት አደረገኝ ነበር ያለችው፡፡

ከዚህ በላይ ኪሳራ ምን አለ? አትሉም? አንድ ከወላጆቹ ጋር በመኾን በባሕር ዳር ገበያ በግ ሲሸጥ ያገኘሁት ብላቴና አትማርም እንዴ? የሚል ጥያቄ አቀረብሁለት፤ “ትምህርት ቤቱን እኮ ዘግተውብናል አለኝ፤ እኔ አሁን ፍየል እና በግ ስጠብቅ ነው የምውለው፤ ግን ትምህርት ቤት መቼ ነው የሚከፈትልን ጋሼ! ናፈቀኝ፤ የታዳጊው ምላሽ እና ጥያቄ ነበር።

ይህ ጥቄ የታዳጊው ብቻ ሳይኾን የሚሊዮን ተማሪዎችም እንደሚኾን የሚጠራጠር ሰው የለም ባይ ነኝ፡፡

በአግባቡ ታርሶ ያልተዘራ እና በእንክብካቤ ያላደገ ሰብል ፍሬያማ እንደማይኾነው ሁሉ ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾነ ዜጋ ደግሞ አፈር እንደ ነካ ስጋ መኾኑ እርግጥ ነው፡፡እየመከነ በመኾኑ ሀገርን ማሻገር አይችልም፡፡

ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው፤ 3ሺህ 736 ትምህርት ቤቶች ወና ቀርተው፤ መምህራን ከሥራቸው ለቀው፤ ሲታገቱ፣ ሲገደሉ ኀብረተሰቡ ቆም ብሎ ለምን? በሚል መጠየቅ ከሁሉም ጤናማ ሰው የሚጠበቅ ነው።

ኧረ ወደየት እየሄድን ነው? በማለት ነገሩ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲኾን በሰላማዊ መንገድ መሞገት ግድ ይላል ብየ አስባለሁ። ሰዓቱ እየረፈደ ቢኾንም ሳይመሽ በክልሉ የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርት እንዲያገኙ በውጭ ሀገራት ያሉ አካላትም የዓለም አቀፍ ተቋማትን ቢሮ ማንኳኳት ይገባቸዋል ባይ ነኝ።

በሀገር ውስጥ ማኅበረሰቡ ትምህርት ሲነካበት ለምን? ማለት አለበት፡፡ የየትኛውም አካል ቀዳሚ ተግባር ትምህርትን ማስቀጠል መኾንም ይገባል፡፡

አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ ሲጠፋበት አብሮ እንደሚቃወመው ሁሉ፤ ከተሜው ስኳር እና ዘይት ሲጠፋበት በኀብረት እንደሚጮኸው ሁሉ ትምህርት ሲጠፋም ሰላማዊ ጩኸትን ማሰማት ያስፈልጋል። ዛሬ ትምህርት ከሌለ ነገ ሁሉም ነገር አይኖርምና።

ትምህርትን ማቋረጥ የአማራ ክልል ሕዝብ ሊቅ፣ አዋቂ፣ ተመራማሪ እና ተወዳዳሪ ልጅ እንዳያወጣ እየተደረገ መኾኑን ሁሉም ወገን ከወዲኹ ቆም ብሎ በማጤን የትምህርትን መቋረጥ መቃወም አለበት።

ትምህርት ቤቶች ይከፈቱ! ተማሪዎች ያለከልካይ ይማሩ! መምህራን በነጻነት ያስተምሩ!

ካልኾነ ግን ትልቁን የአማራ ሕዝብ ከተወዳዳሪነት ማሳነስ እና ነገውን ማበላሸት ይኾናል።

ሠላም!

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሚዲያዎች ሕፃናትን በመልካም ምግባር የማነፅ አደራ አለባቸው።
Next articleየመጀመሪያዋ የሴት ዲፕሎማት!