
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። አምስት ባለድርሻ አካላትን ያካተተው ክልላዊ የአጀንዳ ማሠባሠብ የምክክር መድረክ ሚያዝያ 04/2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል።
በምክክሩ ላይ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት እና ማኅበራት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና በመጀመሪያው ዙር ምክክር ለሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የተመረጡ የወረዳ ማኅበረሰብ ወኪሎች እየተሳተፉ ነው።
መሠረታዊ የአማራ ክልል ሕዝብ አጀንዳዎችን ነቅሰው ማውጣታቸውን የምክክሩ ተሳታፊ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ገልጸዋል። እነዚህ አጀንዳዎች ከዳር እንዲደርሱም የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት ቴዎድሮስ ዘውዱ (ዶ.ር) ከሀገር ውጭ እንደሚኖሩ እና በዚህ ምክክር መድረክ ለመሳተፍ ወደ ሀገራቸው እንደመጡ ጠቁመዋል።
የአማራ ሕዝብ ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ በበርካታ ውሳኔዎች ላይ እንዳይሳተፍ ተገልሎ መቆየቱን ገልጸው ሀገራዊ ምክክሩን ግን እስከ መጨረሻው በንቃት መከታተል እንደሚገባው አስገንዝበዋል። ይህ መድረክ ለሁሉም እኩል ዕድል የሚሰጥ እና ነጻ ውይይትን የሚፈቅድ ኾኖ እንዳገኙትም ተናግረዋል። ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ ነው፤ በዚሁ ቀጥሎ ለሀገር የሚበጅ ሥርዓት ለመገንባት ግብዓት መኾን አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከምድር በላይ እና ከፀሐይ በታች ያሉ ሀገራዊ ችግሮች በሙሉ ተነስተው እንዲመከርባቸው በሩን ከፍቷል። ሕዝቡም ይህንን አምኖ እየተወያየ ነው፤ የክልሉን አጀንዳዎች ለቅመን እየተወያየን ነው፤ መንግሥትም ይህንን ተቀብሎ ከዳር ለማድረስ አደራውን መቀበል አለበት ብለዋል።
በተለይም ታጥቀው ጫካ የገቡ እና በተለያየ ምክንያት የቀሩ ወንድሞች በምክክሩ እንዲሳተፉ ጥሪ መደረጉ እና ዕድሉ መመቻቸቱ ሀገራዊ መፍትሔ ለማግኘት ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል። ይህንን ዕድል መጠቀም ለነገ የማይተው የሁሉም ዜጋ ኀላፊነት ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖች ውይይትን ምርጫ ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ኮማንደር ደመላሽ ካሳየ (ዶ.ር) የምክክር ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻ እና ገለልተኛ ኾኖ እየተካሄደ መኾኑን ታዝቤያለሁ ብለዋል። ሕዝቡም ይሄንን ተገንዝቦ ለዘመናት በውስጡ ያሉ አጀንዳዎችን እያነሳ መኾኑን ተናግረዋል። ይህንን ዕድል ከርቀት ኾኖ ከመመልከት እና ሳያዩት ከመተቸት ይልቅ በንቃት መሳተፍ እና በተግባር ፈትኖ ማየት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሀገራዊ አጀንዳዎችን ማንሳታቸውን እና ለምክክር ኮሚሽኑ እና ለሕዝብ በአደራነት እንደሚሰጡም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ገጥመዋታል፤ ምክክር ለችግሮቿ መፍትሔ ነው፤ ስለዚህ ያለአንዳች ሰበብ ቀርቦ መወያየት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኀላፊነት ነው ብለዋል። ይህ ሀገራዊ ምክክር ሳንጠቀመው ቢያልፍ የሚቆጭ ሀገራዊ ዕድል ነው ሲሉም ገልጸዋል። በውይይቱ በመሳተፍ ሀገርን የሚቃኙ አጀንዳዎችን ማስያዝ እና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ቆሞ መፍትሔ ማበጀት ግድ ይላል ነው ያሉት።
ምሁራን ሁሌም ለሀገራቸው የሚበጅ ሃሳብ እና ዕውቀት ይጠበቅባቸዋል፤ በዚህ ምክክር ላይም ከፊት ቀድመው የመፍትሔ ሃሳቦችን ማመንጨት አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል። ሌላው ከሰሜን ጎንደር ተጉዘው በባሕር ዳር ሲመክሩ ያገኘናቸው የሀገር ሽማግሌ ገብሬ ከፍያለው “ሀገር የምትቆመው በምክክር፣ በውይይት፣ በይቅርታ እና በእርቅ ነው” ብለዋል። ሀገራዊ ምክክሩም የገጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እንደ ሕዝብ የተሰጠ ዕድል ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ መኾን የሌለባቸው በርካታ ችግሮች አልፈዋል፤ የችግሮችን ማብቂያ ጊዜ ለማሳጠር የመመካከሪያው ጊዜ አሁን ነው ሲሉም አስገንዝበዋል። በአፈሙዝ ችግሩን የፈታ ሀገር የለም፤ ይልቁንም ዜጎችን ለሰቆቃ መዳረግ ነው፤ ሰክኖ ከልብ መወያየትን መልመድ ይገባል ነው ያሉት።
ሀገራዊ ምክክሩን ሳያዩ እና ሳይሳተፉ የሚተቹ እና ለማደናቀፍ የሚሞክሩ አካላት ከዚህ ድርጊት እንዲታቀቡ፤ ይልቁንም የሕዝብ መድረክ መኾኑን ተገንዝበው እና ሕዝብን አክብረው ቀርበው መሳተፍ እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
