
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ለመላው የአማራ ሕዝብ እና የአማራ ሕዝብ አጀንዳ ይመለከተኛል ለሚሉ አካላት ጥሪ አቅርቧል። ድርጅቱ በመግለጫው የአማራ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት በተደራራቢ የፖለቲካ እና የጸጥታ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኝ ገልጿል።
ሕዝቡ ላጋጠመው ችግር በሀገር ደረጃ የተጀመሩ የመፍትሄ ፍለጋ ሂደቶችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስቧል። አብን የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በጀመራቸው የአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደቶች ንቁ ተሳታፊ በመኾን የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች የያዙ አጀንዳዎችን ማቅረቡን እና የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውሱን ለማርገብ የሚችሉ የመፍትሄ አማራጮችን በሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እየሞገተ መኾኑን ገልጿል።
በተጨማሪም ድርጅቱ አሁን ላይ የአማራን ሕዝብን ተቋማት ለማፍረስ እና ሕዝቡ አስተባባሪ እና መሪ እንዳይኖረው የሚጥሩ ኀይሎችን ሴራ ለማክሸፍ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል። ከሰሞኑ ባካሄደው የመታደስ ጉባኤም የሕዝቡ ትግል መስመር እንዲይዝ እና ፈጣን ምላሽ እንዲያገኝ ከመቼውም በላይ በኀላፊነት እንደሚሠራ አብን አረጋግጧል።
ይሁን እንጂ የአማራ ሕዝብ የገጠሙት ፈተናዎች ውሥብሥብነትን በመገንዘብ አብን በራሱ ተቋማዊ አቅም ከሚያደርገው ትግል በተጨማሪ ሕዝቡን የማንቃት፣ የማደራጀት እና የማታገል ሥራ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንደሚፈልግ ድርጅቱ አመልክቷል። በአማራ ሕዝብ አጀንዳዎች ዙሪያ የተሠባሠቡ ቡድኖች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀራርበው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል።
የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ጥረቶች እንደ መታገያ መድረክ በመውሰድ ሊነሱ የሚገባቸውን አጀንዳዎች በሙሉ በማስመዝገብ እንዲሳተፉ አሳስቧል። አብን ለዚህ ጥረት አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ እና እገዛ እንደሚያደርግም አረጋግጧል። አብን የአማራ ሕዝብ አጀንዳዎች የእሱ ብቻ እንዳልኾኑ በመገንዘብ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ቡድኖች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ የሙያ ማኅበራት እና የሃይማኖት ተቋማት፣ የባሕል ቡድኖች እና ሌሎች ተቋማት በምክክር ኮሚሽኑ ጥረቶች ውስጥ ዕድሎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርቧል።
የፌዴራል እና የክልል መንግሥታትም የታጠቁ ኀይሎች የምክክሩ አካል እንዲኾኑ አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርጉ አብን አሳስቧል። በመጨረሻም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ሕዝብ አጀንዳዎች በአማራ ክልል ብቻ የተወሰኑ አለመኾናቸውን በመገንዘብ በመላው ሀገሪቱ በሕግ እና በፖለቲካ ተገፍቶ ዘርፈ ብዙ በደሎችን እያስተናገደ ያለው የአማራ ሕዝብ አጀንዳዎቹን እንዲያስመዘግብ ከማድረግ ባለፈ ተፈጻሚነታቸውን እንዲከታተል እና አስቻይ ሥርዓት እንዲያበጅ አብን ጠይቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
