
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) ልጆቻቸው ያለስጋትና መጉላላት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ፣ እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን የቀጠለው የኩበት ጭስ እና ኩራዝ ተረት እንዲሆን እናቶች ሁሉ በሕዳሴ ግድብ ተስፋ ይዘዋል፡፡
ዓባይ አድጎ (ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ) ሊጦራቸው፣ የችግራቸው መፍትሔ ሊሆን፣ ከጭንቀታቸው ሊያጽናናቸው እና ነጋቸውን በብሩህ ተስፋ እንዲጠብቁት ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡
ነዋሪነታቸው ከታላቁ የኢትዮጵያ ወንዝ መነሻ ግሽ ዓባይ ከተማ ነው፡፡ ወይዘሮ አስረሴ ይኖሩበት የነበረው ሰፈር ወደ ከተማው ከመካተቱ በፊት በግብርና ሥራ ይተዳደሩ ነበር፡፡ እንደማንኛውም ኢትየጵያዊ የሀገር ቤት ኑሯቸውን ሲገፉ የቆዩት እኝህ ሴት የሚያርሱት መሬት ወደ ከተማው ስለተካተተባቸው ከግብርና ሥራቸው ውጪ ከኑሮ ጋር የሚያደርጉት አሰልቺ ትንቅንቅ መርሯቸው ‘ነገ የተሻለ ይሆንልኛል’ የሚል ተስፋ ሰንቀዋል፤ ይህ ተስፋቸው ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው፡፡
በግብርና ሥራ በሚተዳደሩበት ጊዜ ዓባይ ወንዝን በስፋት የሚጠቀሙት ለጸበል፣ ለመታጠቢያ እና ለከብቶቻቸው መጠጥ ብቻ ነበር፡፡ እርሳቸው እና የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ወንዙን እምብዛም ለግብርና ሥራ ጥቅም ላይ አላዋሉትም፡፡ ተጠቀሙ ከተባለም በጀሪካን ቀድቶ ችግኝ የማጠጣት ያኽል እንጂ በሥርዓት ገድበው በበቂ ሁኔታ አላመረቱበትም፡፡ እንደ ባላደራ ዓባይን ከምንጩ በሥርዓት ተንከባክበው በመጠበቅ የትውልድ ቀየውን (ግሽ ዓባይን) ጥሎ ሲሰናበታቸው የስደት ጉዞውን ፈቅደው በስስት ይሸኙታል እንጂ ከሕይወት ጋር ለገጠሙት ግብግብ ድል መንሻ መሳሪያ አድርገው አልተጠቀሙትም፡፡
ከአምስት ዓመታት ወዲህ የወይዘሮ አስረሴ ኑሮ ከእሳት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ እሳትን የሚጠቀሙት ምግብ ለማብሰል ብቻ ሳይሆን ከኑሯቸው ጋር የሚያደርጉትን አሸናፊ አልባ ትንቅንቅ ለመጋፈጥም ጭምር ነው፡፡ የ10 ልጆች እናት ናቸው፤ ከእነዚህ መካከል ስድስቱ የግል ሥራ ስለሌላቸው የሕልውና መሠረታቸው እናታቸው አረቄ አውጥተው በሚያገኙት ጥሪት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሥራቸውን የሚያከናውኑት ደግሞ ማገዶ በመግዛት ነው፡፡ ወሮታቸው አነስተኛ ገቢ ማግኘትና እና ከፍተኛ የጤና ጉዳት ቢሆንም ለምግብ ማብሰያ በወር እስከ 1 ሺህ ብር፣ ለአረቄ ማውጫ ደግሞ በየቀኑ እስከ 400 ብር አውጥተው ማገዶ ይገዛሉ፡፡
ወይዘሮ አስረሴ ከገጠር ኑሮ ወደ ከተሜነት መለወጥን አጥብቀው የጠሉት ለምን ይሆን?
ኑሯቸው ከእሳት ጋር ከተቆራኘበት ጊዜ ጀምሮ በተለያየ መልኩ ለችግር ተጋልጠዋል፡፡ በአንድ በኩል በግብርና ሥራ አምርተው ልጆቻቸውን በቀላሉ ሲያስተዳድሩ የነበሩት እናት አረቄ ሸጠው በሚገዙት አስቤዛ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የኢኮኖሚ እጥረት በእጅጉ ተፈታትኗቸዋል፡፡ ኑሯቸው በሸመታ አስቤዛ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሕይወታቸውን ማሻሻል ቢያቅታቸው እንኳን ያለውን ለማስቀጠል በሚያደርጉት ጥረት በተደጋጋሚ ለጤና ችግር ተጋልጠዋል፡፡ ልጃቸውን ለማስተማር እና ለማሳደግም በአንድ ጊዜ ስድስት ማድጋ (እንስራ) ጥደው ነው አረቄ የሚያወጡት፡፡ የእሳት ወላፈን የሰውነተታቸውን ወዝ አደብዝዞ ፊታቸውን አበልዞ ከሰውነት ተራ አንዳወጣቸው አብረናቸው ቆይታ ባደረግንበት ጊዜ ታዝበናል፡፡ እርሳቸውም በጢስ እና ሙቀት ምክንያት ለተደጋጋሚ የጤና ችግር እንደሚጋለጡ ነግረውናል፡፡ የወላድ አንጀታቸው በስድስት ልጆቻቸው ሥራ አጥነት ተጨንቆ ስለቀጣይ የሕይወት ዕጣ ፈንታቸው አብዝቶ ያሳስባቸዋል፡፡
የወይዘሮ አስረሴ ሕይወት ስለግብፃውያን እናቶች ሕይወት እንድናስብ ያስገድደናል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ግብፃውያን በሚባል ደረጃ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ስለሆኑ፡፡ የግብጽ የኤሌክትሪክ ሽፋን ከ99 በመቶ በላይ መሆኑ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡ በጣም አስቸጋሪ ገጠራማ ቦታዎች ካልሆኑ በስተቀር በገጠርም ሆነ በከተማ የኤሌክትሪክ ሽፋን ተደራሽ አድርጋለች፡፡ ታዲያ ግብጽ ያለች አንዲት እናት እና በወይዘሮ አስረሴ መካከል ሊኖር የሚችለውን ልዩነት መገመት ይከብዳል? የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ሽፋን ከፍተኛ ከሆነ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እንዲነቃቃ፣ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲያድግ የጎላ አስስዋጽዖ ይኖረዋል፡፡ ከኃይል ማመንጫዎቿ መካከል አንዱና ዋንኛው ደግሞ የአስዋን ግድብ ነው፡፡ አስዋን ግድብ የተሠራው ከኢትዮጵያ (ወይዘሮ አስረሴ ከሚኖሩበት ግሽ ዓባይ) ከሚመነጨው ጥቁር ዓባይ እና ከሱዳኑ ከነጭ ዓባይ ጥምረት ከናይል ወንዝ ነው፡፡ የጥምረቱ 85 በመቶ ከኢትዮጵያ ከሚነሳው ጥቁር ዓባይ የሚመነጭ ነው፡፡
በአንጻሩ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋን ከ44 በመቶ አልበለጠም፡፡ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባገኘነው መረጃ መሠረት እስከ 2025 ዓ.ም ድረስ ሁሉንም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ተደራሽ ማድረግ እና በ2030 ዓ.ም ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ታዲያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ይህንን እውን ለማድረግ ድርሻው የጎላ ነው፡፡
ወይዘሮ አስረሴም ግልገል ዓባይ አድጎ (ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ) ሊጦራቸው፣ የችግራቸው መፍትሔ ሊሆን፣ ከጭንቀታቸው ሊያጽናናቸው እና ነጋቸውን በብሩህ ተስፋ እንዲጠብቁት ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከድሀ መቀነታቸው አንስተው እየደገፉ መሆኑን ነግረውናል፡፡
ግድቡ ሲጠናቀቅ በከተማው ያለው የመብራት ችግር ተቀርፎ የኤሌክትሪክ ምድጃ እንደሚጠቀሙ፣ ልጆቻቸው በተለያዩ የሥራ መስክ ተሰማርተው ራሳቸውን እንደሚችሉላቸው፤ እንደሚጦሯቸውም ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ በሳምንት፣ በሁለት ሳምንት ሲበዛም ደግሞ ከዚያም በላይ የሚታየው የመብራት መጥፋት መፍትሔ የሚያገኘው የዚያን ጊዜ እንደሚሆንም አስበዋል፡፡ የነዳጅ ወፍጮ በኤሌክትሪክ ተቀይሮ የወፍጮ ቤት ዋጋ እንደሚቀንስላቸው (የወፍጮ ቤቱን የክፍያ ውድነት ሁለቴ እንደመሸመት ያህል ይቆጥሩታል)፣ ከግዥ ማገዶ መላቀቅ ብቻ ሳይሆን ከተሠማሩት አድካሚ ሥራ እፎይ የሚሉባትን ቀን በጉጉት እየተጠባበቁ ነው፡፡
“ዓባይ የልጆቼ የኅልውና መሠረት፣ የመጦሪያ ተስፋዬ ነው!” በማለትም ሕልማቸው እውን ሆኖ ለማየት አቅማቸው በፈቀደ መጠን ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ “መንግሥት ግድቡን ለእኛ ያድርግልን እንጂ እኛም ያቅማችንን ከማድረግ ወደኋለላ አንልም!” በማለትም የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቷን ዳር ድንበር አስከብሮ ሕዳሴ ግድቡን የማስጨረስ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ሙሉ እምነት ጥለዋል፡፡ አሁን ያለው ትውልድም እንደ ቀድሞዎቹ ኢትዮጵያውያን የሀገርን ሉዓላዊነት የማስቀጠል እና ክብሯንም ከፍ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡