
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የበይነ መረብ ዓውዱ እና ውስብስብ ፍላጎቶች የፈጠሩትን የድኅረ እውነት ወቅት ፈተና ለመቋቋም የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ሥራውን ከተለመደው መንገድ በማውጣት ወደ ዓላማ ተኮር ማሸጋገር እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ (ዶ.ር) አስገነዘቡ፡፡
“ዓላማ ተኮር ተግባቦት ለኢትዮጵያ መንሰራራት” በሚል መሪ መልዕከት ለክልል እና ለከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መሪዎች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ በሚገኘው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ላይ ነው ሚኒስትሩ ይህንን ያስገነዘቡት፡፡ የበይነ መረብ አውዱ የመረጃ ፍሰቱን ከአንድ ወደ ባለብዙ አቅጣጫ የቀየረ እና የመረጃ ስርጭት ፍጥነቱንም በእጅጉ ያሳደገ በመኾኑ ይህንን ሁኔታ ያገናዘበ የመንግሥታዊ መረጃ ስርጭት መኖር እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡
ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ምልዓተ ሕዝቡን ለመድረስ የኮሙዩኒኬሽን ሥራችን ዓላማ ተኮር ማድረግ፤ በስትራቴጂ መምራት እና ሁሉንም የተግባቦት አማራጮች በመጠቀም የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት ማሟላት ልናተኩርባቸው የሚገቡ ናቸው ብለዋል፡፡ የአገልግሎቱ ሚኒስትር ድኤታ ከበደ ዴሲሳ ደግሞ የኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ ከሚዲያ ጋር ያለውን ግንኙነት በመግራት በአጀንዳ የመምራት ኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
በኮሙዩኒኬሽን መዋቅሩ እና በሚዲያ መካከል ጤናማ፣ በዕቅድ የሚመራ እና የኢትዮጵያን መሻት የሚያሳካ መስተጋብር መኖር አለበት፡፡ በሁለቱ ዘርፎች መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከር የመንግሥት እና ሕዝብ ፍላጎቶችን ለማገናኘት፤ ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞችን እና መዳረሻ ትልሞችን ለማስረጽ ያስችላል ነው ያሉት።
የኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ሚዲያውን በአጀንዳ በመምራት የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን እና የመረጃ ብክለትን በመቀነስ የመንግሥትን አኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሁለንተናዊ አቅጣጫዎች በመልዕክቶች አማካኝነት እንዲያስገነዝብ፤ በውጤቱም ምልዓተ ሕዝቡን እንዲያሳትፍ አቶ ከበደ አሳስበዋል፡፡
በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ከመጋቢት 29/2017 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ባለው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ከ220 በላይ የክልል እና የከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መሪዎች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዘርፉን በመረጃ ሥርጭት እና አጀንዳ ከማቀናጀት እና ማናበብ በተጨማሪ በአቅም ግንባታ ሥራዎች ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተደጋጋሚ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
