
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ሦስተኛው የብየዳ ሙያ ዓመታዊ ጉባኤ ከሚያዚያ 6/2017 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 8/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የዓለም አቀፍ የቴክኖሎጅ ማምረት እና ብየዳ ልህቀት ማዕከል አስታውቋል።
የዓለም አቀፍ የቴክኖሎጅ ማምረት እና ብየዳ ልህቀት ማዕከል ኀላፊ ሰላሙ ይስሃቅ (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫ ጉባኤው በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም እንደሚካሄድ ገልጸዋል። ጉባኤው እና የብየዳ ውድድሩ “አፍሪካን ማብቃት፣ የብየዳ አቅምን ማጎልበት፣ ለቀጣናዊ ትብብር እና ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪነት” በሚል መሪ መልዕክት የሚካሄድ ይኾናል።
በዚህ ዓመታዊ ጉባኤ እና ውድድር ላይ ከ16 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች እንደሚሳተፉም ይጠበቃል። ዶክተር ሰላሙ እንደገለጹት ጉባኤው እና ውድድሩ በብየዳ ሥራ ዙሪያ የተሠሩ ጥናት እና ምርምሮችን እንዲኹም የልምድ ልውውጦችን ለማካሄድ ያለመ ነው።
ብየዳ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዘርፍ ላለው ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የተናገሩት ዶክተር ሰላሙ በተለይም በትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን አብራርተዋል። በዚህ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ከተሳታፊ ሀገራት ጋር በዘርፉ የልምድ ልውውጥ እንደምታደርግም ተናግረዋል።
በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ 43 ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ ሲኾን ለተሻሉ ተወዳዳሪዎችም የተለያዩ ሽልማቶች እንደሚሰጡ ተገልጿል።
ከኢትዮጵያ 21 ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉም ታውቋል።
በአዲስ አበባ ቆይታቸው ተሳታፊዎቹ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየምን፣ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤትን፣ የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን እና የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን እንደሚጎበኙም በመግለጫው ላይ ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
