ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ሁሉም መተባበር አለበት።

26

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ ተግባር ለመከላከል ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ሊረባረብ እንደሚገባ የከተማዋ የደንብ ማስከበር መምሪያ አስታውቋል። ወይዘሮ እናት ዓለምነህ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ሲኾኑ በመጠጥ እና ምግብ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው ለስምንት ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

በየዕለቱም የንግድ ተቋማቸውን ሙሉ ለማድረግ ከቤታቸው ገበያ እንደሚባትሉ አስታውሰዋል። በሥራ ሂደትም በታክሲ ፌርማታ ላይ በሚፈጠር ወከባ በተደጋጋሚ ለዝርፊያ መዳረጋቸውን አንስተዋል። ሌላው በባሕር ዳር ከተማ የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪ መኾናቸውን የተናገሩት አቶ ተስፋ ጥሩነህ ግለሰቦች በጠራራ ጸሐይ መንገድ አስቁመው እንደፈተሿቸው እና የያዙትን ተንቀሳቃሽ ስልክ የይለፍ ቁልፍ ማስከፈታቸውን ተናግረዋል።

ሕገ ወጦች የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚ አለመኾኔን ካረጋገጡ በኋላ ስልኩ በባለሙያ መፈተሽ አለበት በሚል ዘረፉኝ ነው ያሉት። “እኔ ‘ከዘራፊዎች’ ጋር እሰጣ አገባ ስገጥም የደረሰልኝ ሕግ አስከባሪም ኾነ ግለሰብ ባለመኖሩ ከተንቀሳቃሽ ስልክ በተጨማሪ በቦርሳየ የነበረውንም ጥሬ ገንዘብ ወሰዱብኝ” ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሙያ ሃምሳ አለቃ ሰጠኝ አንዳርጌ በከተማዋ ሰዎች በየዕለቱ በሕገ ወጦች እንደሚታለሉ አስታውሰዋል። እኛ ሕግ ለማስከበር 24 ሰዓት በፈረቃ እየሠራን ነው የሚሉት የሃምሳ አለቃ ኀብረተሰቡ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር እጅ እና ጓንት ኾኖ ከሠራ ሕገ ወጥነትን በቀላሉ ማምከን ይቻላል ይላሉ።

ደንብ አስከባሪው ሃምሳ አለቃ ሰጠኝ አክለውም ሕገ ወጦችን አደብ ለማስያዝ እና ሕገ ወጦችን ለሕግ ለማቅረብ የኀብረተሰቡ ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል። ተባብረን ከሠራን ሕገ ወጥ ድርጊትን በመቆጣጠር ባሕር ዳር ከተማ ሰላሟ የተጠበቀ እንዲኹም የሰዎችም ኾነ የንግድ እንቅስቃሴዋን ጤናማ ማድረግ አይሳነንም ነው ያሉት።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ደንብ ማስከበር መምሪያ ኀላፊ ኃይለሚካኤል አርዓያ የደንብ ማስከበር መምሪያ ዋናው ተልዕኮ ሕገወጥነትን መከላከል ነው ብለዋል። ሕገወጥነትን መከላከል ለአንድ ተቋም ብቻ የሚሰጥ ተግባር አይደለም የሚሉት አቶ ኃይለሚካኤል ሁሉም አካላት በመተባበር፣ በመተጋገዝ ፣ በመደጋገፍ እና በመነጋገር ቢሠራ ውጤታማ መኾን ይቻላል ነው ያሉት።

ኀብረተሰቡ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር ከተባበረ ዘረፋን፣ ሕገ ወጥ ንግድን፣ መንገድ መዝጋትን፣ የመሬት ወረራን፣ ሕገ ወጥ ግንባታን እና ሌሎች መሰል ሕገ ወጥ ተግባራትን መከላከል ቀላል ነው ብለዋል መምሪያ ኀላፊው።

ባሕር ዳር ከተማ የሕግ አስከባሪዎችን በቁጥርም በአደረጃጀትም አጠናክራለች ያሉት መምሪያ ኀላፊው ለሕግ አስከባሪዎች የተለየ የደንብ ልብስ በማልበሷም ኀብረተሰቡ ራሱን ከአጭበርባሪዎች በቀላሉ መለየት ይቻላል። በመኾኑም በርካቶችን ከዘረፋ መታደግ ያስችላል ነው ያሉት።

የደንብ አስከባሪውን ኀይል ልዩ ልዩ የጸጥታ ተቋማት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ማኀበረሰቡ ከጎኑ ኾኖ ከደገፈው ወንጀልን መከላከል ቀላል እንደሚኾን መምሪያ ኀላፊው አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleስጋት የፈጠረው ኮሌራ!
Next articleሦስተኛው የአፍሪካ የብየዳ ሙያ ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ከቀናት በኋላ ይካሄዳል።