
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኮሌራ በዓይን በማይታይ ባክቴሪያ ተህዋሲያን አማካኝነት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ በአብዛኛው በተበከለ ውኃ ይተላለፋል። የተበከለ ውኃ መጠጣት፣ የተበከለ ምግብ መመገብ፣ የግል እና የአካባቢ ንጽህና ጉድለት (ሜዳ ላይ ወይንም ከሽንት ቤት ውጭ መጸዳዳት፣ መጸዳጃ ቤቶችን በአግባቡ አለመጠቀም) ለኮሌራ በሽታ አጋላጭ ምክንያቶች ናቸው።
በድንገት የሚከሰት የሩዝ ውኃ የሚመስል አጣዳፊ ተቅማጥ፣ ማቅለሽለሽ፣ በተደጋጋሚ ማስመለስ ደግሞ ምልክቶች ናቸው። በሰውነት ውስጥ ያለው ፈሳሽ እየቀነሰ ሲሄድ ደግሞ የአቅም ማነስ፣ የቆዳ መሸብሸብ፣ የዐይን መሰርጎድ እና የአፍ መድረቅ ያስከትላል፡፡ በፍጥነት ሕክምና ማግኘት ካልተቻለ በአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውኪያ አማካይነት በሰውነት ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ ማዕድናት ከፈሳሽ ጋር አብረው ስለሚወጡ ለሞት ጭምር ይዳርጋል።
መከላከያ መንገዶች፦
ንፁህ ውኃ መጠጣት፣ እጅን በሳሙ እና በንፁህ ውኃ መታጠብ፣ መጸዳጃ ቤቶችን በአግባቡ መጠቀም፣ የምግብን ንጽህና መጠበቅ፣ ውኃን አፍልቶ እና አቀዝቅዞ መጠጣት ወይም በውኃ ማከሚያ ኬሚካል የታከመ ውኃ መጠቀም፣ የአካባቢ ንጽህናን በአግባቡ መጠበቅ፣ ምግብን በሚገባ አብስሎ ከተቻለ በትኩስነቱ መመገብ ይገባል።
ከቤት የሚወጡ ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻዎች አካባቢን እና ውኃን እንዳይበክሉ በአግባቡ ማስወገድ ይገባል።
የበሽታው ምልክት የሚታይባቸውን ሰዎች ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋም ማድረስ ከተቻለ ደግሞ በቀላሉ መዳን የሚችል በሽታ ነው።
የበሽታው አኹናዊ ኹኔታ፦
ኮሌራ በአማራ ክልል ከሐምሌ/2015 ዓ.ም ጀምሮ ተከስቶ 4ሺህ የሚኾኑ ሰዎች ተጠቅተዋል። በሽታው ከሌላ ክልል ተነስተው ወደ ክልሉ በገቡ ተጓዦች አማካይነት እንደገባ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ገልጸዋል።
ሥርጭቱን ለማስቆም በተሠራው ሥራ በአጭር ጊዜ መቆጣጠር ተችሎ እንደነበር አንስተዋል። ሥርጭቱን ማስቆም ከተቻለባቸው ምክንያቶች ደግሞ የሰዎችን ጉዞ መገደብ አንዱ ነበር።
በ2017 ዓ.ም ደግሞ በሽታው ከታኅሣሥ ጀምሮ ዳግም ተከስቶ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መዛመቱን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት። በሽታው በመጀመሪያ በምዕራብ ጎንደር ዞን በቋራ ወረዳ “በርሚል” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ተከስቶ አኹን ላይ ወደ ሰሜን ጎጃም፣ ባሕር ዳር ከተማ እና አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኮሌራ ሕሙማን ሪፖርት መደረጉን ገልጸዋል።
እስከ መጋቢት 28/2017 ዓ.ም 1ሺህ 446 ሕሙማን ሪፖርት ተደርጓል፤ የሰዎች ሕይዎትም አልፏል ነው ያሉት።
አንዳንድ የጸበል ቦታዎች የሚያስተናግዱትን የሰው ቁጥር ታሳቢ ያደረገ የንጽሕና መጠበቂያ ሥራ ባለመሥራታቸው ለሽታው መስፋፋት በምክንያትነት ተቀምጧል።
ከዚህ በፊትም በእነዚህ አካባቢዎች በተለይም ደግሞ በምዕራብ ጎንደር ቋራ ወረዳ በበርሚል አካባቢ አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ባለመቋረጡ ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት ኾኗል ነው ያሉት።
አኹን ላይ በሽታውን ለመከላከል ኢንስቲትዩቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የተጠቁ ሰዎችን በመለየት ሕክምና እና የንጽሕና አገልግሎት እየተሠጠ መኾኑን ገልጸዋል።
ይኹን እንጅ የመጸዳጃ እና የውኃ አቅርቦት ላይ አኹንም ችግር መኖሩን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ የተከሰተውን በሽታ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እንዲቻል ረጅ ድርጅቶች እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
ማኅበረሰቡም የአካባቢውን እና የግል ንጽሕናውን እንዲጠብቅ፣ በሽታው ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚያደርገውን ጉዞ ደግሞ እንዲያቆም መክረዋል።
የሃይማኖት አባቶች በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለተወሰነ ጊዜ እንዲያቋርጡ ጠይቀዋል። የጉዞ ወኪሎችም ከሚያደርጉት ያልተገባ ቅስቀሳ እንዲታቀቡም አሳስበዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል። በሽታው ወደ ከፋ ደረጃ ተሸጋግሮ ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት መንግሥት የጉዞ ክልከላ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በአንዳንድ ሰዎች በጸበል ቦታዎች በሽታው እንዳልተከሰተ የሚተላለፈው መረጃ የተሳሳተ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀጣይ ኢንስቲትዩቱ አጠቃላይ ስለወረርሽኙ እየተከታተለ አስፈላጊውን መግለጫ እንደሚሰጥም ነው የገለጹት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
