
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በሻህ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነትን እና ተጠቃሚነትን ለማሳካት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያቀረበችው ማብራሪያ ዲፕሎማሲያዊ ስኬትን አስገኝቷል።
ፕሮፌሰሩ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ የጣሊያን ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር እንዳትደርስ ለማድረግ ያለመ ሴራ ሠርተው እንደነበር ጠቅሰዋል።
አኹን ላይ ኢትዮጵያ ትናንት በግፍ ያጣችውን የባህር በር ተጠቃሚነት መብቷን ለማስከበር ዓለም አቀፍ ሕግን በጠበቀ እና ሰላማዊ በኾነ መንገድ ስትራቴጂ ነድፋ እየሠራች እንደኾነ ፕሮፌሰር ብሩክ ተናግረዋል።
የአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት በአፍሪካ መስፋፋት እና አዳዲስ ግዛቶች መፈጠር ኢትዮጵያ የነበራትን የባህር በር እንድታጣ ምክንያት እንደኾነም አስረድተዋል።
የባህር በር የሌላት መኾን ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ እያስከተለ መኾኑንም ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር ብሩክ ሀገሪቱ ያጣችውን ሀብት ለማግኘት በሰላማዊ እና ግልጽ መንገድ በመንቀሳቀስ እንዲኹም አካሄዷን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስረዳት ረገድ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቧን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምትከተለው ሰላማዊ እና ግልጽ አካሄድ ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቅሰዋል።
ፕሮፌሰሩ የባህር በር የሌላት ሀገር ሉዓላዊነት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በመገንዘብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጀመረው ሰላማዊ የተጠቃሚነት መብት እንዲሳካ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
