
ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መጭውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል እየሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል።
መምሪያው መጭውን በዓል ምክንያት በማድረግ ዘይት እና ሌሎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ ምርቶችን ለማኅበረሰቡ ማቅረቡን ገልጿል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኅላፊ ዮሴፍ መለሰ መጭውን የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ጤናማ የሆነ የግብይት ሂደት እንዲኖር ከዩኒዬኖች እና ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ 20 ሺህ ሊትር ዘይት፣ መኮረኒ፣ ፓስታ እና ሌሎች መሠረታዊ ምርቶችን ለማኅበረሰቡ መቅረቡንም ገልጸዋል።
በከተማው ያለውን የገበያ ሥርዓት ሊያረጋጉ የሚችሉ የባዛር ዝግጅቶች ለማዘጋጀት እና የእርድ እንስሳትን ከሌሎች አካባቢዎች በማምጣት ለማኅበረሰቡ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
ሸማቹ ማኅበረሰብ በባለቤትነት ያልተገባ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን በማጋለጥ መብቱን ሊያስከብር እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የንግዱ ማኅበረሰብ በበዓል ወቅት ሰላማዊ የኾነ የግብይት ሂደት እንዲኖር የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
