
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፍያ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ከስምንት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ለአንድ ሰዓት የሚቆይ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ የሙሉ አቅም ልምምድ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ልምምድ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ እና የእርዳታ መስጫ ቁሳቁሶች ብቁነትን፣ በአደጋ ጊዜ የሚኖር የመልዕክት ልውውጥ ፍሰትን እና በእርዳታ ሰጪዎች መካከል የሚኖረውን ቅንጅት እና ጥምረት ለመፈተሸ ይረዳል፡፡
በተጨማሪም ልምምዱ ከአየር ማረፍያው ውጪ የሚገኙ እርዳታ ሰጪዎች ከአየር ማረፍያው አቀማመጥ እና በውስጡ ከሚገኙ የእርዳታ መስጫ ቁሳቁሶች ጋር እንዲተዋወቁ በማድረግ በእውነተኛ ድንገተኛ አደጋ ወቅት የእርዳታ አሰጣጥ ሂደቱ የተፋጠነ እንዲሆን በማስቻል ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ይህንንም ለመፈተሽ በወቅቱ በከተማው ሆስፒታሎች እና በአየር ማረፍያው መካከል የእርዳታ መስጫ ተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴ የሚኖር መሆኑን እያሳወቅን ይህ እንቅስቃሴ የልምምዱ አካል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንዲረዱልን በታላቅ አክብሮት እንገልፃለን።
አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፍያ መሰል ልምምዶችን በየሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ያከናውናል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
