ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ለፌዴሬሽኑ አቤቱታ አቀረበ፡፡

257

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ2012 ዓ.ም ሁሉም የሊግ ውድድሮች እንዲቋረጡ መወሰኑ ቅሬታዎች እየተነሱበት ነው፡፡

የዓለም ስጋት የሆነው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለም ከመዝናኛ ውጭ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ መዝናኛው ራስን ከድብርት ለማራቅ ከማስቻሉም በላይ ለሚሊዮኖች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ ለበርካታ ሀገራት ደግሞ እንደ አንድ የኢኮኖሚ አውታር ሆኖም ያገለግላል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ2012 ዓ.ም ሊግ ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዝ ማድረጉ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ እና በከፍተኛ ሊግ የሚሳተፉ ቡድኖች ተቃውሟቸው ከፍ ብሏል፡፡ በጥሩ ፉክክር ውስጥ ሆኖ ሊጠናቀቅ 13 ጨዋታዎች ቀርተውት የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የድካም ዋጋ ሳያገኝ መቋረጡ ነው ቡድኖችን ቅር ያሰኘው፡፡

በእርግጥ የመሪዎቹ እና የተከታዮቹ የነጥብ ልዩነት ጠባብ መሆን ጨዋታው ቢካሄድ ዋንጫውን ማን ይወስደዋል የሚለውን ማወቅ ባያስችልም ጨዋታዎች እስኪቋረጡ ድረስ ውድድሩን በውጤት ሲመሩ የነበሩትን ቡድኖች ቅር አሰኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን “በርካታ አማራጮችን ከተመለከትኩ በኋላ የደረስኩበት ነው” ባለው ውሳኔው ሊጉ ያለምንም ሽልማት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡ ሲቋረጥም እንደሌሎች ሀገራት የሊግ አሸናፊውን፣ ወደ ታችኛው የሚወርደውን፣ ከታችኛው ወደ ላይኛው ሊግ የሚመጣውን እና አህጉራዊ ተሳታፊ ቡድኖችን ሳይለይ ነው ውድድሩ ልክ ምንም እንዳልተካሄደ በመቁጠር የሰረዘው፡፡ በዚህ ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑት ቡድኖችም ቅሬታዎቻቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ የባሕርዳር ከነማን ቅሬታ በተመለከተ ከሰሞኑ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድንም ውሳኔውን በመቃወም “የቅሬታ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ አስገብቻለሁ” ብሏል፡፡ የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ማኅበር ሊቀ መንበር ኃይለማርያም ፈረደ “የስታዲዬም ገቢ ለቡድናችን መሠረት ነው፡፡ ውድድሩ በመቋረጡ ደግሞ ይህን አጥተናል፤ የደጋፊዎቻችን ዓላማ ፋሲል ከነማ ዋንጫ እንዲያነሳ ነው” ብሏል፡፡ ይህን በማሰብም ደጋፊዎች ወደ ሩቅ ቦታዎች ሳይቀር በመሄድ በተለያዩ ሜዳዎች እየተዘዋወሩ ቡድናቸውን ሲያበረታቱ እንደነበር አስታውሷል፡፡ ለቡድኑ የገቢ ድጋፍ የሚሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት የተያዙ ዕቅዶች በወረርሽኙ ምክንያት መቋረጣቸውንም ተናግሯል፡፡ በዚህ ምክንያትም ቡድኑ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያጣ ነው የተናገረው፡፡ ውሳኔው በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በደጋፊዎቻቸው ሥነ ልቦና ላይም ተፅዕኖ እንዳለው ገልጧል፡፡

የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ሥራ አስኪያጅ አብዮት ብርሃኑ አቤቱታቸውን ለማሰማት የቡድኑ ቦርድ ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ‘‘የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮዎች አንጻር ሲታይ ትክክለኛ እንዳይደለም’’ ተናግረዋል፡፡ “ሊጉ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከተቋረጠ በመቋረጡ ቅሬታ የለንም፤ ነገር ግን የሚገባንን ማግኘት አለብን” ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡ ጨዋታዎቹ ተቋረጡ ከተባለም እስኪቋረጥ ድረስ ሊጉን ሲመራው የነበረው ቡድን የሚገባውን ነገር ማግኘት እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ወደ ውሳኔ ከመሄዱ በፊት ቡድኖችን እንዳላማከረ በመጥቀስም ሀገሪቱን ወክለው የሚሳተፉት ቡድኖችን መለየት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ካፍ “ውሳኔያችሁን አሳውቁኝ” ባለበት በጨረሻው ቀን መወሰኑ ሌላው የቅሬታ ምንጭ ነው፡፡ ምንም እንኳን ፌዴሬሽኑ የቀጣይ ዓመት ውድድሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? በሚለው ጉዳይ ያስቀመጠው ሐሳብ ባይኖርም ቡድኑን በገንዘብ ለማጠናከርና ወሳኝ ተጫዋቾችን ለማቆዬት ከወዲሁ ፕሮጀክት ተነድፎ እየተሠራ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጊዜያዊ ዋና ጸሐፊ ባሕሩ ጥላሁን ውሳኔው የመጨረሻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ውሳኔውን ያሳለፈውም የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነው፤ ምን አልባት የመታዬት ዕድል ካለውም ሊያየው እና ሊያሻሽለው የሚችለው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ነው” ብለዋል፡፡ ከውሳኔው በፊት ውድድሩን የማስሄድ ዕድል ካለ ስፖርት ኮሚሽን እና የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን እንደጠየቁም አስታውቀዋል፡፡ ከጤና ሚኒስቴርም ምክረ ሐሳቦችን መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡ “ሀገሪቷ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ስላለች ውድድሩን ለማስኬድ የሚያስችል መንገድ አልነበረም፤ ውድድሩ ቀጣይ ዓመት እንዲደረግም ሐሳብ ቀርቦ ነበር፤ ነገር ግን አህጉራዊ ውድድሮች የሚካሄዱት ከዚያ አስቀድሞ ስለሆነ ሀገሪቱን የሚወክሉትን ለመምረጥ አስቸጋሪ ነው፤ ስለሆነም ውሳኔው የሚያስደስት ባይሆንም እንዲቋረጥ ሆኗል” ብለዋል አቶ ባሕሩ፡፡ የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮዎችን እንዳዩም ተናግረዋል፤ ውድድራቸውን ያቋረጡ ሀገራት አሸናፊውን የለዩት ጥቂት ጨዋታዎች ስለቀሩና የነጥብ ልዩነታቸው ሰፋፊ ስለነበር እንደሆነ አብነት ጠቅሰዋል፡፡ “የውድድሩ 75 በመቶ ጨዋታዎች ከተካሄደ እስኪቋረጥ ድረስ ሲመራ የነበረው ቡድን አሸናፊ ይሆናል’ በሚለው የሌሎች ሀገሮች ሕግ ለመሄድ ቢታሰብም የእኛ ጨዋታ ከዚያ ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ 75 በመቶ ካልደረሰ ደግሞ ‘በመጀመሪያው አጋማሽ ውጤት ይታያል’ በሚለው ሕግ ብንሄድ እንኳን ውሳኔው ሁሉንም የሚያስማማ ስላልሆነ መቋረጡ የመጨረሻ አማራጭ ነው” ብለዋል ዋና ጸሐፊው፡፡

ከቡድኖች ጋር ለምን አልተወያያችሁም? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር የፕሪሚዬር ሊጉ አስተዳደርና ሥራ አስፈጻሚ የመወሰን ስልጣን እንዳለው ተናግረዋል፡፡ “የስፖርት ባለሙያዎች ሊያዩት የሚችለውን ዕይታ ሁሉ ዓይተናል፤ ያን የማድረግ ችግር የለብንም” ብለዋል፡፡ ወረርሸኙ በቁጥጥር ስር የሚውልበት ጊዜ ስለማይታወቅ የ2013ዓ.ም የውድድር ዘመንም ስጋት ውስጥ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ቡድኖች በገንዘብ እጥረት ደመወዝ የመክፈል ችግር እና የመፍረስ አደጋ እንዳይከሰትባቸው መንግሥትን እንደጠየቁና መልሱ አዎንታዊ ሊሆን እንደሚችል በተስፋ እየጠበቁ መሆናቸውንም አቶ ባሕሩ አስታውቀዋል፡፡ የዓለም እግር ኳስ የበላይ ጠባቂ ፊፋ የአደጋ ጊዜ በጀት እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውንም ተናግረዋል፡፡ በጀቱ ከተለቀቀ ቡድኖችን ለማገዝ እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበሶማሊያ የተከሰተ ጎርፍ 24 ሰዎችን ለሞት ዳርጎ ከ280 ሺህ በላይ ሰዎችን አፈናቀለ፡፡
Next articleየትልቁ ወንዝ ልጆች የውኃ ጥማት …፡፡