የእምቦጭ አረምን በርብርብ ማስወገድ ካልተቻለ ዘርፈ ብዙ የብዝኅ ሕይዎት አደጋ እንደሚያስከትል የዘርፉ ተመራማሪ ተናገሩ፡፡

22

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የደልጊ ዙሪያ ነዋሪ የኾኑት አቶ ወርቁ እንየው አምስት የቤተሳብ አባላትን ዓሳ በማስገር እንደሚያስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡ ”ጣና ሐይቅ ሕይዎታችን ነው ” የሚሉት አቶ ወርቁ ዓሣ ከማስገር ባለፈ በቀላሉ የሐይቁን ውኃ በመጠቀም በመስኖ እያለሙ የሚኖሩ በርካታ የአካባቢው ነዎሪዎች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የጣና ሐይቅ በእምቦጭ አረም በመወረሩ በታንኳም ኾነ በጀልባ ተንቀሳቅሶ ዓሳ ለማስገር መቸገራቸውን አቶ ወርቁ ተናግረዋል፡፡ በመስኖ ልማቱ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩንም እንዲሁ፡፡ የእምቦጭ አረም የዓሳዎችን እንቅስቃሴ በመገደቡ ዓሳዎች ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰደዱ እያደረገ ነው የሚሉት አቶ ወርቁ በሐይቁ ውስጥ ያለው የዓሳ ሃብት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመቀነሱ በኑሯቸው ላይ አደጋ መደቀኑን ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ትሁኔ አስረስ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የወራሚት ገብርኤል ቀበሌ ነዋሪ ሲኾኑ ዓሣ ከአስጋሪዎች በጅምላ እየተቀበሉ በመበለት ለገበያ በማቅረብ ቤተሰብ እንደሚያስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡ ዓሳ በበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቢፈለግም ከዓመት ወደ ዓመት ምርቱ እየቀነሰ በመምጣቱ ገቢያቸው ቀንሶ ለችግር መዳረጋቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃ እና ልማት ቡድን መሪ እያየኝ ብርሃኔ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በእነርሱ አካባቢ የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ ጥሩ ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት፡፡ በወቅቱም በውስን ቦታ ብቻ የነበረውን አረም በኅብረተሰብ ተሳትፎ የመከላከል ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ እስከ 2014 ዓ.ም ድረስም ”ጣና ሐይቅ የእኔ” ብሎ የሚሠራ ማኅብረሰብ ለመፍጠር የተደረገውን ውጤታማ ርብርብ አስታውሰዋል። በ2015 ዓ.ም 1 ሺህ 689 ሄክታር መታረሙንም አቶ እያየኝ ተናግረዋል፡፡

አሁን ክልሉ ያጋጠመው የሰላም እጦት የመከላከል ሥራውን አቀዛቅዞታል ያሉት አቶ እያየኝ በአራት ወረዳዎች እና በ18 ቀበሌዎች የነበረው አረም አሁን ላይ በ8 ወረዳዎች እና 21 ቀበሌዎች የሐይቁን 3 ሺህ 522 ሄክታር ሸፍኖታል ብለዋል፡፡ በችግር ውስጥ ኾኖም ኅብረተሰቡን በማስተባበር 1 ሺህ 462 ሄክታር የእምቦጭ አረምን ማስገድ መቻሉን አቶ እያየኝ ተናግረዋል፡፡

የጣና ሐይቅን መጠበቅ የእያንዳንዳችንን ሕይዎት ከመጠበቅብም በላይ ነው ያሉት አቶ እያየኝ ጣናን የመጠበቅ ጉዳይ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፤ በመኾኑም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት እንዲሁም ኅብረተሰቡ በንቅናቄ የጣናን ሕልውና የመጠበቅ የሞራልም የዜግነትም ግዴታ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ጉዳዩ መኖርና ያለመኖር መኾኑን አቶ እያየኝ ጠቁመዋል፡፡

የጣና እና ሌሎች የውኃ አካላት ልማት እና ጥበቃ ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ዳዊት አቡ በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋው የእምቦጭ አረም 5 ሺህ ሄክታር ሸፍኗል ነው ያሉት። እስካሁንም ከ1 ሺህ 500 ሄክታር በላይ የሰው ጉልበት እና ማሽንን በመጠቀም አረሙን ማስወገድ ተችሏል ነው የሉት፡፡

አረሙ በስምንት ወረዳዎች እና በ30 ቀበሌዎች ተስፋፍቷል ያሉት ምክትል ሥራ አሥኪያጁ ባለፉት ዓመታት አረሙን ለማስወገድ በተከናወነው ሥራ የሚፈለገውን ውጤት ባለማስገኘቱ የችግሩን ሥፋት አሳሳቢ አድርጎታል። የኮቪድ በሽታ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ክልሉ የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለአረሙ መስፋፋት በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

የእምቦጭ አረምን ለማስገድ ሰፊ የማኀበረሰብ ንቅናቄን እና ከፍተኛ ሃብት ይጠይቃል ያሉት አቶ ዳዊት ከተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ግድ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ሳይንሳዊ የኾነ አዋጭ እና ሀገር በቀል መፍትሄ ማምጣት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጤ እና ተስፋፊ ዝርያ ክትትል እና ቁጥጥር ተመራማሪ መዝገብ ዳኜው ጣና ሐይቅ ቅርስ በመኾኑ ሁሉም በርብርብ ሊጠብቀው ይገባል ነው ያሉት። ሐይቁ በብዝኀ ሕይዎት የበለጸገ ነው የሚሉት ተመራማሪው በባሕር ዳር ከተማ ዳርቻ ጭምርም በእምቦጭ ተወርሯል ብለዋል።

ማኅበረሰቡን በማስተባበር ረገድ ችግር አለ ያሉት ተመራማሪው ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የሥራ ኀላፊዎች አረሙን ለማስወገድ በቁርጠኝነት ተረባርበው ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየብዙዎች ፈተና!
Next articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ