
ደሴ: ሚያዝያ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ገምግሟል። በግምገማው በመደበኛ እና በሕግ ማስከበር ተግባራት ላይ በዘጠኝ ወሩ የተከናወኑ ተግባራት ላይ ውይይት ተደርጓል።
የሰላም አሥከባሪ አባል የኾኑት 50 አለቃ ወንድወሰን ጌታሁን የደሴ ከተማን ሰላም ለማስጠበቅ በመቶም ኾነ በጓድ በመደራጀት ከሕዝቡ ጋር ቅንጅት በመፍጠር ሌት ከቀን እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ሌላው የሠራዊቱ አባል ሙስጠፋ ሰይድ ደሴ እና አካባቢው ሰላም እንዲኾን በትጋት እየሠሩ መኾኑን እና ከዚህ አልፎም በአጎራባች አካባቢዎች የሰላም ማስከበር ግዳጃቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሻለቃ አለባቸው አስፋው የውይይት መድረኩ የዘጠኝ ወር አፈጻጸምን ከመገምገም ባለፈ በአዲስ አደረጃጀት በክልሉ የሚሰጠውን ማንኛውንም ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁነት የሚገልጹበት እንደኾነ ነው ያስገነዘቡት።
የደሴ ከተማ ሰላም አስከባሪ እና ሚሊሻ ከደሴ ከተማ ሕዝብ፣ ከደሴ ዙሪያ እና ከደቡብ ውሎ ሕዝብ ጋር በጋራ በመኾን እና ከአጋር የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት ባለፉት ወራት በጉጉፍቱ፣ በማርዬ ስላሴ እና አምባሰል ግዳጃቸውን በተገቢው መልኩ መወጣታቸውን ተናግረዋል።
በግዳጅ አፈጻጸማቸው አንጸባራቂ ድል ማስመዝገባቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ሕዝባቸውን 24 ሰዓት በንቃት እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ በዘጠኝ ወራት የደሴ ከተማን ሰላም ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
በቀጣይም ይህንን ለማስጠበቅ እና አጠናክሮ ለመሄድ ከፖሊስ እና ሰላም አስከባሪ ኀይሉ ጥምረት ባለፈ ከመከላከያ ሠራዊት እና ከአጎራባች የደቡብ ወሎ እና የኮምቦልቻ ከተማ አካባቢዎች ጋር ቅንጅታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ ፡-መሐመድ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
