
ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በትኩረት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የሰሜን ሸዋ ዞን አስታውቋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ተክለየስ በለጠ ከአሚኮ ደብረ ብርሃን 91 ነጥብ 4 የኤፍ ኤም ጣቢያ የማዕዘን ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች በርካታ ሕዝባዊ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰዋል።
በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶችም የዞኑ ሕዝብ ለሰላም መስፈን ቁርጠኛ አቋም እንደያዘ አረጋግጠናል ነው ያሉት። ከአጎራባች የዞን አሥተዳደር መዋቅሮች ጋር በተሠራ ጠንካራ ግንኙነት ከአሁን በፊት ሲያጋጥሙ የነበሩ የሰላም መደፍረስ ችግሮችን ማስቀረት መቻሉንም አንስተዋል። በዚህም በጸጥታ መደፍረስ ችግር ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን የመመለሱ ሥራ በመከናወን ላይ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የጸጥታውን ችግር ሰበብ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የሚፈጥሩ ሰበበኛ የሥራ ኀላፊዎችን ዞኑ እንደማይታገስም አስገንዝበዋል። ለሚፈጠረው ብልሹ አሠራር እና ለሚመዘገበው ስኬትም መሪዎች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ያሉት ምክትል አሥተዳዳሪው ይህንን ኀላፊነት ወደ ጎን በመተው ለግል ጥቅም ያደሩትን በመረጃ ክትትል እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል ብለዋል።
አሁን ባለው የተሻለ ሰላማዊ እንቅስቃሴ አማካኝነት ተፈናቃዮችን ከመመለስ ጀምሮ ጾም የሚያድሩ መሬቶችንም ለዘር ዝግጁ እንዲኾኑ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ዞኑ አስተማማኝ ሰላም ላይ እንዲደርስም በየደረጃው ያለ መሪ እና ማኅበረሰቡ በቅንጅት በመሥራት ለውጤት እንድረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
