የውስጥ ጥንካሬ እና ዐቅም ለውጭ ግንኙነት ስኬታማነት ፋይዳው ትልቅ ነው።

23

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የውስጥ ጥንካሬ እና ዐቅም ለውጭ ግንኙነት ስኬታማነት ፋይዳው የላቀ በመኾኑ በዚህ ላይ አተኩሮ መሥራት እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገልጸዋል፡፡

“ዓላማ ተኮር ተግባቦት ለኢትዮጵያ መንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት ለኮሙኒኬሽን ዘርፉ የክልል እና የከተማ አሥተዳደር መዋቅር መሪዎች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ ያለው ሥልጠና በሁለተኛ ቀን ውሎው ጂኦ-ፖለቲካዊ ዓውዶች እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ አተኩሮ ተሰጥቷል፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ውስጣዊ ዐቅሞችን ማጎልበት ለውጭ ግንኙነት ስኬታማነት የላቀ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል። የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ እነዚህን ዐቅሞች ለማጎልበት የተቀረጹ ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን ማስገንዘብ እና ማስረጽ ላይ እንዲያተኩር አሳስበዋል፡፡

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን፣ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን፣ የመንግሥት መነሣሣቶችን በአግባቡ ማስገንዘብ፣ ቀጣናዊ እና ዓለማቀፋዊ አዝማሚያዎችን እና አንድምታቸውን የተመለከቱ ወቅታዊ እና ሚዛናዊ መረጃዎችን መስጠት ለሀገራዊ ገጽታ መገንባት እና ለዲፕሎማሲ ስኬት ፋይዳቸዉ ጉልህ መኾኑን ነው ያብራሩት፡፡

በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች የተቀናጁ፣ የተደራጁ እና ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት ዜጎች የሀገራቸውን ፍላጎት እና ዕቅድ ተገንዝበው በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ዲፕሎማት እንዲኾኑ ማስቻል ይገባል ብለዋል፡፡ አዲሱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እሳቤ ወቅታዊ ነባራዊ ዓውዱን ያገናዘበ፣ ለኢትዮጵያ ሕልሞች መሳካት ከውስጥ ወደ ውጭ የሚያይ እና ቅድሚያ ለጎረቤት የሰጠ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡

በተለይ ዜጋ ተኮር የሚለው አዲሱ ዕይታ በተለያዩ ሀገራት በሰቆቃ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው መመለስ እንዳስቻለ አውስተዋል። የሥልጠናው ተሳፊዎች ለዘርፉ በተከታታይ እየተሰጡ ያሉ የፖሊሲ እና የዐቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ጥልቀት ያለው ግንዛቤ እየፈጠሩ፣ ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት ለማሳካት እያስቻሉ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleነውራል ኔትወርክ (የነርቭ አውታር መረብ) ምንድን ነው?
Next articleበጸጥታ ችግር ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖች የመመለሥ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አስታወቀ።