
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ስናወራ ሁለት ንዑስ ክፍሎች አብረው ይነሳሉ። እነዚህም ማሽኖችን የማስተማር ሂደት እና ጥልቅ አስተውሎት ናቸው። ለሁሉም ጥላ የኾነው ጽንሰ ሃሳብ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ነው።
ጠቅለል ባለ መንገድ የሰዉ ሠራሽ አስተውሎት ኮምፒውተር ሳይንስን እና ዳታን በመጠቀም ማሽኖች ችግር ፈች ለኾነ አገልግሎት እንዲውሉ የሚያደርግ ሰፊ ሳይንስ ነው።
ንዑስ ክፍል ተብሎ የተገለጸው ማሽኖችን የማስተማር ሂደት (Machine Learning) ኮምፒውተሮችን በበርካታ መረጃዎች በማለማመድ ተግባራትን እንዲያከናውኑ የምናደርግበት ሳይንስ ነዉ።
ዲፕ ለርኒንግ ያልነው ደግሞ ማሽኖችን በማስተማር ሂደት ውስጥ የሚካተት ኾኖ ነውራል ኔትወርክን (የነርቭ አውታር መረብን) የሚጠቀም ነው። ውስብስብ እና ብዛት ያለውን መረጃ (ዳታ) ለመተንተን እና ችግሮችን ለመፍታት አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ሦስት ነጥቦች ነውራል ኔትወርክ ምንድነው? የሚለውን ለመረዳት መሠረት የኾኑ ናቸው:: ሌላው ጽንሰ ሃሳቡን ለመረዳት የምናቀርበው የሰው ልጅ አዕምሮ ውስጥ ያሉ ነውሮኖች የሚሠሩበት መንገድ ነው::
የሰው ልጅ አዕምሮ በቢሊዮን የሚቆጠሩ እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ እና በኤሌክትሪካዊ እና ኬሚካላዊ ሲግናል ተግባቦት የሚያደርጉ ኒውሮኖች አሉት። ነውራል ኔትወርክም እርስ በርስ በተሳሰሩ ሰው ሠራሽ ነውሮኖች (ኖድስ) አማካኝነት መረጃን የሚያቀናብር ሥርዓት ነው።
ነውራል ኔትወርክ ግብዓትን የሚቀበልበት፣ የሚያቀነባብርበት እና ውጤት የሚያመነጭበት ሂደት አለው፡፡ የሚፈለግ ተግባርን እንዲሠራልን ውጤቱ ምን መኾን አለበት የሚለውን እንዲያውቅ ቅድሚያ የማስተማር (ማሽን ለርኒንግ ) ሂደትን ያልፏል።
በዚህ ሂደት ካለፈ በኋላ ራሱን ችሎ መረጃን በማቀነባበር ውስብስብ ተግባራትን ለማከናወን የሚችል የጥልቅ አስተውሎት አይነት ነው ነውራል ኔትወርክ (የነርቭ አውታር መረብ)።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
