“ሁሉም አሸናፊ ኾነው የሚወጡበትን ዐውድ ለመፍጠር ምክክሩ አስፈልጓል” ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር)

43

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ክልል አጀንዳ ማሠባሠብ ሁለተኛውን ምዕራፍ እያካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) እንዳሉት ምክክር እስካኹን የተፈጠሩ ችግሮችን ዋነኛ ምንጭ ለመለየት እና መፍትሔ ለማስቀመጥ የሚካሄድ ነው።

መፍትሔ ላይ የሚደረሰው ደግሞ በጠብመንጃ፣ በዱላ እና አላስፈላጊ ቃላትን በመወራወር ሳይኾን በምክክር መኾኑን ገልጸዋል። በምክክር ጸንቶ መቆም እንደሚቻል ደግሞ የዓለም ታሪክ ማሳያ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ኮሚሽነሩ በምክክሩ አስፈላጊ ያሏቸውን ነጥቦችም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሰላማዊ መንገድ መመካከር ባሕል ማድረግ አንዱ ነው። ልዩነቶችን ተቀራርቦ በሰላም መፍታት ለዘላቂ ሰላም እና ለሀገር አንድነት ግንባታ ሚናው የጎላ መኾኑንም ነው የገለጹት።

ሌላኛው አስፈላጊነት ደግሞ ሕግ እና ሥርዓትን ለማስፈን መኾኑን አብራርተዋል። አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር መመካከር ማስፈለጉንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ውድድር አሸናፊው ሁሉን የሚወስድበት ሳይኾን ሁሉም አሸናፊ ኾነው የሚወጡበትን ዐውድ ለመፍጠር ምክክር አስፈላጊ መኾኑን ነው የጠቆሙት።

በውይይቱ የተገኙ ባለድርሻ አካላትም አጀንዳ በመስጠት በተለይም መዋቅራዊ ችግሮች ምንጫቸውን በመለየት፣ ችግሮችን በሚገባ መግለጽ የሚችሉ መሪዎችን ለሀገራዊ ጉባኤው በመምረጥ እና በመመካከር፣ በመነጋገር እና በመከባበር መሠረታዊ የዴሞክራሲ ልምምድን በተግባር እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የሚሄድበት አሠራር የለውም” ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም
Next articleነውራል ኔትወርክ (የነርቭ አውታር መረብ) ምንድን ነው?