“የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የሚሄድበት አሠራር የለውም” ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም

46

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል እያደረገ የሚገኘውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ሁለተኛ ምዕራፍ ማካሄድ ጀምሯል። በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች እና ሌሎች የክልሉ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በኢትዮጵያ ሀገራዊ ሰላም እና አንድነት እንደሚያመጣ ታምኖበት በተጀመረው ምክክር እምነት አሳድራችሁ ስለመጣችሁ እናመሰግናለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎችን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሲያሰባስብ መቆየቱን ገልጸዋል። ለአሳታፊነት እና አካታችነት ትኩረት በመስጠት የሃሳብ ውክልና እንዲኖር ሠርቷል፤ እየሠራም ይቀጥላል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ከመጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ተወካዮችን የመምረጥ ሥራ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ከወረዳዎች የተወከሉ ተወካዮች ባለፉት ቀናት በስኬት አጀንዳቸውን ማጠናቃቀቸውን ገልጸዋል።

የማይቻል የሚመስሉ ውጣ ውረዶችን አልፈው ይሄን ታሪካዊ ኀላፊነት የተወጡ የክልሉ የማኅበረሰብ ወኪሎች ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት። የአማራ ክልል ጉዳይ መላው የአማራ ክልል ሕዝብ የሚያገባው መኾኑን መገንዘብ ይገባል ያሉት ኮሚሽነሩ ሰሞኑን በተሳተፉት የማኅበረሰብ ወኪሎችም ይህንን ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።

የክልሉ ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው የተባሉትን አንስተው አስመዝግበው መመለሳቸውንም ገልጸዋል። በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው የምክክር ሂደት እጅግ ከፍተኛ ክንውን የተመዘገበበት፣ በቀጣይም የሚመዘገብበት ነው ብለዋል። ለየት ያለ አጀንዳ አለን፣ ልንሰማ ይገባል ለሚሉ ሁሉ ሂደቱ የሚያስተናግድ እንደኾነ እናረጋግጣለን ነው ያሉት።

“የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የሚሄድበት አሠራር የሌለው መኾኑ ታውቆ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የዚህ ታሪካዊ ሂደት አካል መኾን እንደሚችሉ እናረጋግጣለን” ብለዋል።

በእስር ቤት ያሉ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ጫካ የገቡ፣ ሀገራቸውን ለቀው በሌሎች ሀገራት የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ሁሉ ሃሳባቸውን የሚሰጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ኮሚሽኑ ቁርጠኛ መኾኑ እናሳውቃለን ነው ያሉት። አጀንዳዎችን ለመቀበል ሁልጊዜ ዝግጁ መኾኑንም ገልጸዋል።

በጫካ የሚገኙ ወገኖች በምክክሩ እንዲሳተፉ ጥረቶችን እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። በምክክር ያልተፈቱ የሃሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች በጠላትነት ለመፈረጅ በር ከፋች የመኾን እድላቸው ሊያበቃ ይገባል ብለዋል።

እስካሁን የከፈልነው ዋጋ ከልክ ያለፈ ነው፣ ለምንስ አንድ ሰው ይሙትብን? ለምንስ እናቶች በሀዘን ይኮራመቱብን? ለምንስ ሲባል ወላጅ ያለ ጧሪ ይቅር? ለምን ሲባልስ የኢትዮጵያ ወጣቶች ተስፋቸው ይጨልም? ለምንስ ድህነት ቤቱን ይሥራብን? ነገ ሳይኾን ዛሬ በቃን ልንል ይገባል ብለዋል።

ሀገር የሚያቆመው ሰው ነው፣ ሀገርም የምትጸናው በልጆቿ የሃሳብ ልዕልና እና ትልቅነት ነው፣ ኢትዮጵያውያን የችግሮቻችን መንስዔ ለመለየት ተከባብረን እና ተደማምጠን መመካከር እና መግባባት ላይ ለመድረስ ከማንም የምናንስ ሕዝቦች አይደለም ነው ያሉት። ይልቁንም ይሄን ባሕል ቀድመን ለዓለም ያሳወቅን ነን እንጂ ብለዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ በንቃት በመሳተፍ ኢትዮጵያን በጋራ በመገንባቱ ሂደት የበኩሉን አሻራ የማሳረፍ ታሪካዊ አደራ እና ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት።

በሁለተኛው ምዕራፍ የሚሳተፉ ተሳታፊዎች ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል። በየእለቱ አዳዲስ ቅራኔዎችን እያወጡ፣ ልዩነቶችን እያሰፉ መከራችን ለማስረዘም የሚሠሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ክልል የባለድርሻ አካላት ክልላዊ የምክክር መድረክ ተጀመረ።
Next article“ሁሉም አሸናፊ ኾነው የሚወጡበትን ዐውድ ለመፍጠር ምክክሩ አስፈልጓል” ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር)