
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም እና ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን የአጀንዳ ማሰባሰብ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ በጥሩ ኹኔታ መቀጠሉንም ገልጸዋል።
ሀገራችን በአንድነት የምትቀጥለው ሁላችንም ተባብረን ሥንሠራ ነው ብለዋል። ሚዲያ ሀገርን የመገንባት ትልቅ ሚና አለው ያሉት ኮሚሽነሩ ሚዲያዎች እያደረጉት ላለው ሥራ ምስጋና አቅርበዋል። አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባሩ ከቅዳሜ መጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ ባማረ እና በደመቀ መልኩ እየሄደ ነው ብለዋል። የተሳታፊዎች ሥነ ምግባር የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከየወረዳው የመጡ ተሳታፊዎች ሲያካሂዱት የሰነበቱት ምክክር ሥርዓት ያለው እና ግልጽነት የተመላበት ነበር ነው ያሉት። ተሳታፊዎች ምን ያክል ለሀገራቸው እንደሚያስቡ እና ምን አይነት ጠንካራ አጀንዳ ሲያነሱ እንደነበር ተመልክተናል ብለዋል። ሂደቱ አሳታፊነት፣ ግልጽነት እና አካታችነት ያለው መኾኑንም ገልጸዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው ግልጽነት የተሞላበት፣ ዜጎቻችን ምን ያህል ደረጃ ላይ እንደደረሱ ያየንበት ነው ብለዋል። በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ትምህርት የወሰድንበት እና የዜጎቻችን ታላቅነት ያየንበት ነው ብለዋል። “ዜጎች ፈተና እና መከራ ሳይበግራቸው ትልቁን ምስል አሳይተዋል” ነው ያሉት። ባሳዩት ነገር ተደንቄያለሁ፣ ትልልቅ አጀንዳዎችን ሲያቀርቡ ነው የተመለከት ነው፣ ለሀገር የሚጠቅም አጀንዳ ነው ሲመርጡ የሰነበቱት ነው ያሉት። ውጤታማ የኾነ ሂደት መከናወኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) በምክክር ሂደት ሚዲያ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል። በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው አጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ በጥሩ ኹኔታ እየቀጠለ መኾኑንም ገልጸዋል። የእስካኹኑ አካሄድም የሚያስደንቅ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር ምክክር ባሕል መኾን አለበት ነው ያሉት። ኢትዮጵያን ምክክር ብቻ እንደሚያወጣት በተደጋጋሚ ማስተማር እንደሚገባም ገልጸዋል። አኹን ታላላቅ ሥራዎች እንደሚቀሩ የተናገሩት ኮሚሽነሩ የመመካከር ባሕል ግንባታ የሁላችንም የቤት ሥራ ነው ብለዋል።
የመደማመጥ፣ የመከባበር እና የመመካከር ባሕልን ለልጆቻችን ማውረስ አለብን ነው ያሉት። ስለ ሰላም መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ ችግሮችን ተቋቁሞ ያደረገው ነገር የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል።
ተሳታፊዎች ያቀረቧቸው አጀንዳዎች በተገቢው መንገድ ለምክክር እንደሚቀርቡም ገልጸዋል። አንድም አጀንዳ ዝም ብሎ የሚተው አለመኾኑንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
