
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) ምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሶማሊያ የጎርፍ አደጋ ከሰሞኑ እየተመላለሰባት ነው፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽሐፈት ቤት እንዳስታወቀው ሰሞነኛው ጎርፍ በሶማሊያ የ24 ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል፤ 283 ሺህ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው አፈናቅሏል፡፡
መረጃዎቹ እንደሚያመላክቱትም በሶማሊያ በ28 አውራጃዎች ከ701 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፉ ቀጥተኛ ተጎጅ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ሂርሸበሌ፣ ጁባላንድ እና ደቡብ ምዕራብ ግዛቶች ከ88 በመቶ ያላነሱ ተጎጅዎች ያሉባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ የፑንትላንድ አንዲት አነስተኛ ከተማ በጎርፉ በከፊል ተጠራርጋ መወሰዷም ታውቋል፡፡
ማስተባሪያ ጽሕፈት ቤቱ እንዳለው ደራሽ ጎርፍ ነው አደጋውን እያስከተለ ያለው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ደራሽ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደሉንና ማፈናቀሉንም ዘገባዎች እያመለከቱ ነው፡፡
በኬንያ ናይሮቢ የአየር ሁኔታ ፕሮፌሰሩ ክሪስ ሺሳንያ ለሮይተርስ እንደተናገሩት የሕንድ ውቅያኖስ መሞቅ ያስከተለው ርጥበት አዘል ነፋስ በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ዝናብ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፤ ይህም ጎርፍ እያስከተለ ነው፡፡
በጎርፉ ኬንያ ከቀጣናው ሀገራት ክፉኛ ተመትታለች፤ እስካሁን ድረስም 237 ሰዎችን በጎርፉ ተነጥቃለች፤ ከ161 ሺህ በላይ ደግሞ ተፋቅለዋል፡፡ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት በቀጣናው ሀገራት 250 ሰዎች ነበር በጎርፍና በመሬት መንሸራተት ሕይወታቸው ያለፈው፤ ዘንድሮ ግን ከሚያዝያ ጀምሮ ባለው ጥቂት ጊዜ ውስጥ ኬንያ ብቻ 237 ሰዎችን ማጣቷ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ አመላካች ሆኗል፡፡
አሁን ላይ ሶማሊያ በሦስት አስቸጋሪ ፈተናዎች ቅርቃር ውስጥ እንደሆነች የሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ አመላክቷል፤ ጎርፍ፣ የኮሮና ወረርሽኝ እና የበረሃ አንበጣ ናቸው እየፈተኗት የሚገኙት፡፡ እርግጥ ነው ሁሉም ፈተናዎች ለመላው የቀጣናው ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ስጋት ናቸው፡፡ በሶማሊያ ላይ ግን እንደሚበረቱ ተሰግቷል፡፡
በአብርሃም በዕውቀት
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡