ከ51 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በሴፍትኔት መርሐ ግብር ተጠቃሚ ማድረጉን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

36

ጎንደር: ሚያዝያ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሴፍትኔት መርሐ ግብር ከ51 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምግብ ዋስትና እና ሴፍትኔት ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

በመርሐ ግብሩ ጽዱ እና ማራኪ አካባቢዎች መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል። በተግባሩ የጎንደር ከተማን ውበት በመጠበቅ የደረቅ ቆሻሻን በተገቢው መንገድ የማስወገድ እና የማስዋብ ሥራ እየተሠራ ነው።

በከተማዋ በሴፍትኔት መርሐግብር የሥራ ዕድል ተጠቃሚዋ ርስቴ ነጋሽ የከተማዋን ጽዳት ለመጠበቅ በሚያስችል ልክ እየሠሩ ኑሯቸውን እየመሩ መኾኑን ነግረውናል።

ከማኅበረሰቡ ጋር በመናበብ የከተማዋን ውበት ለመጠበቅ እና ጽዱ አካባቢን ለመፍጠር እየሠሩ ገቢ ማግኘት እንደቻሉም የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የኾኑት አቶ ዩሐንስ ደምሴ ጠቁመዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምግብ ዋስትና እና ሴፍትኔት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀድያ መሀመድ 124 ሚሊዮን ብር በመመደብ የሴፍትኔት ተጠቃሚዎቹን ኑሮ ለማሻሻል እየተሠራ ነው ብለዋል። ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር የከተማዋ ጽዳት እና ውበት እንዲጠበቅ መሠራቱንም ገልጸዋል።

በከተማዋ ከ51 ሺህ በላይ ሰዎች የሴፍትኔት ተጠቃሚ መኾናቸውን ኀላፊዋ አንስተው የተጠቃሚዎቹን የቁጠባ ባሕል ማሳደግ እንደተቻለም ተናግረዋል።

23ሺህ ተጠቃሚዎች 18 ሚሊዮን ብር በመቆጠብ ተጠቃሚ መኾን እንደቻሉም ገልጸዋል።

የከተማዋ ማኅበረሰብ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱን በማሻሻል የከተማዋን ውበት ለመጠበቅ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም መልዕክት ተላልፏል።

ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበእደ ጥበብ ሥራ ተጠቃሚ መኾናቸውን በጎንደር ከተማ በሴፍትኔት መርሐ ግብር ታግዘው ወደ ሥራ የገቡ ተጠቃሚ ሴቶች ገለጹ።
Next articleዜጎች ፈተና ሳይበግራቸው ትልቁን ምስል አሳይተዋል።