ፍትሕን ፍለጋ የሚንከራተት ማኅበረሰብ ሊኖር እንደማይገባ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አሳሰበ።

25

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና እውቅና ለመስጠት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 298/2017 ዓ.ም ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የባሕል ፍርድ ቤቱ ግቡን ይመታ ዘንድ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ክልሉ ሰፊ ባሕል እና ወግ ያለው ማኅበረሰብ የሚገኝበት ነው ብለዋል። ባሕል እና ወጉንም እንደ ዕድል መጠቀም እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

በሕዝቦች መካከል መበቃቀል እና የፍትሕ መናጋት እንዳይኖር የባሕል ፍርድ ቤቱ መሠረት ኾኖ ማገልገል እንደሚችልም ተናግረዋል። አሁን ላይ ባሕሎች እና ወጎች እየተሸረሸሩ መጥተዋል ያሉት ቢሮ ኀላፊው ለዚህ መፍትሄ በመኾን በኩል የባሕል ፍርድ ቤቶች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

እንደ ክልል ልክ ያልኾነ አልሸነፍም ባይነት እና አጓጉል ጀብደኝነት የተጠናወታቸው ግለሰቦች እየተበራከቱ መኾናቸውንም ጠቁመዋል። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እና እንቁ የኾነውን ባሕል እና ወግ ጠብቆ ለማዝለቅ የባሕል ፍርድ ቤቶች አማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶች ናቸው ነው ያሉት።

በዚህ ዘመን ላይ ኾነን ፍትሕን ፍለጋ የሚንከራተት ማኅበረሰብ ሊኖረን አይገባም ብለዋል ቢሮ ኀላፊው። ችግሩን በአካባቢው የግጭት መፍቻ መንገድ በመጠቀም የመፍታት ባሕልን ማሳደግ እንደሚገባም ነው የገለጹት። መደበኛ ሕጉም የባሕል ፍርድ ቤቶችን በሚገባ እንዲደግፍ ይደረጋል ነው ያሉት።
የባሕል ፍርድ ቤቱም የማኅበረሰቡን ባሕል እና ወግ በሚያሳድግ እና በሚጠብቅ መልኩ እንዲኾንም ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

ተስፍ የተጣለበት የባሕል ፍርድ ቤቱ ውጤታማ እንዲኾን እና ፍሬ እንዲያፈራ ባለድርሻ አካላት በርትተው ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ባሕልን የፍትሕ ምንጭ ማድረጉ ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም በመድረኩ በአጽንኦት ተነስቷል። የወጣውን አዋጅ ወደ ተግባር ለማስገባት እና ተግባራዊ ለማድረግ በቀጣይ ዝርዝር መመሪያዎች እንደሚወጡም ተገልጿል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የአሚኮ የግቢ ልማት ለሌሎች ማስተማሪያ የሚኾን ነው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleበእደ ጥበብ ሥራ ተጠቃሚ መኾናቸውን በጎንደር ከተማ በሴፍትኔት መርሐ ግብር ታግዘው ወደ ሥራ የገቡ ተጠቃሚ ሴቶች ገለጹ።