“የአሚኮ የግቢ ልማት ለሌሎች ማስተማሪያ የሚኾን ነው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

79

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮሮፖሬሽን (አሚኮ) በከተማ ግብርና ለሌሎች የግል እና የመንግሥት ተቋማት አርዓያ መኾን የሚያስችለውን ሥራ እንዳከናወነ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የግብርና ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፍ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር ) ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ያሉ አንዳንድ ተቋማት የሚያከናውኑት የግቢ ልማት ተሞክሮ ሊወሰድባቸው የሚችሉ መኾናቸውን ያስታወሱት ዶክተር ድረስ አሚኮን ከሌሎች ተቋማት በዋናነት የሚለየው ያለውን ባዶ ቦታ ሁሉ በአግባቡ ለልማት ማዋሉ ነው ብለዋል፡፡

አሚኮ ”በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ” እንዲሉ ግቢውን በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት መሸፈኑ ከሌሎች ተቋማት ለየት ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡ በመኾኑም አሚኮ በግቢ ልማቱ ሠራተኛውን በአትክልት እና ፍራፍሬ ተጠቃሚ አድርጎታለል ብለዋል፡፡

ዶክተር ድረስ የአሚኮ የግቢ ልማት ለሌሎች ተቋማት ማስተማሪያ ሊውል ስለሚችል ግብርና ቢሮ በቀጣይ ሙያዊ ድጋፍ እንደሚሰጥም አስገንዝበዋል፡፡

የግል እና የመንግሥት ተቋማት አካባቢያቸውን በአረንጓዴ አሻራ ሲሸፍኑ በተጠና እና ተጨማሪ ጥቅም ሊሠጥ በሚችል መልኩ መኾን እንዳለበት ገልጸው ተቋማት ከአሚኮ ትምህርት ሊወስዱ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮሮፖሬሽን (አሚኮ) ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ ግቢውን ለሥራ ምቹ ለማድረግ እንዲኹም በአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ተጠቃሚ ለመኾን ታስቦ እየለማ ነው ብለዋል፡፡

ዋና ሥራ አሥፈጻሚው አሚኮ በግቢው ያስቆፈርነውን ጥልቅ ውኃ በመጠቀም አካባቢውን በማልማት ከወዲሁ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ማግኘት ጀምረናል ነው ያሉት፡፡

ግብርና ቢሮ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን የተናገሩት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው የበለጠ ወጤታማ የግቢ ልማትን ለማስቀጠል አሚኮ እንደሚተጋም አረጋግጠዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን እገዛ ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ።
Next articleፍትሕን ፍለጋ የሚንከራተት ማኅበረሰብ ሊኖር እንደማይገባ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አሳሰበ።