የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን እገዛ ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ።

21

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ከተሰጠው ተግባር እና ኀላፊነት በተጓዳኝ ማኅበራዊ ኀላፊነቱንም እየተወጣ እንደሚገኝ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ብርሃኑ ጣምያለው ገልጸዋል።

ኀላፊው እንዳሉት ኮርፖሬሽኑ በክልሉ የሚመረተውን የግብርና ምርት እሴት በመጨመር ለገበያ ማቅረብ የሚችሉ የኢንዱስትሪ ማዕከላትን እያስፋፋ ነው። ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ለበርካታ ወጣቶችም የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ተደርጓል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ከተሰጠው ተግባር እና ኀላፊነት በተጓዳኝ ማኅበራዊ ኀላፊነቱንም እየተወጣ ይገኛል። ዛሬም በባሕር ዳር ከተማ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው 200 የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አድርጓል። ድጋፉ ከ336 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ለእያንዳንዳቸው 10 ኪሎ ግራም የፊኖ ዱቄት እና 3 ሊትር የምግብ ዘይት ነው።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ የኢንዱስትሪ መንደሮችን በማልማት አምራች ኢንዱስትሪው ለሚያደርገው መዋቅራዊ ሽግግር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ተቋም ነው።

ተቋሙ ከተሰጠው ተልዕኮ ባሻገር በየዓመቱ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል። ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያደረገው ድጋፍ አንዱ ማሳያ መኾኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ውስጥ ቅድስት አለነ አንዷ ሲኾኑ ከዚህ በፊት በስፓርታዊ ውድድሮች ላይ ይሳተፉ እንደነበር ተናግረዋል። አሁን ላይ ክልሉ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከአጋጠማቸው የአካል ጉዳት ጋር ተንቀሳቅሶ መሥራት ባለመቻላቸው ቤተሰባቸውን ለመምራት መቸገራቸውን ገልጸዋል። የተደረገው ድጋፍ ያጋጠመውን እለታዊ ችግር የሚቀርፍ መኾኑንም አብራርተዋል።

በቀጣይ በቋሚነት መሥራት የሚችሉበት ዕድል ላይ ትኩረት እንዲደረግ ጠይቀዋል። ሌላኛው ድጋፍ የተደረገላቸው የሻምበል ባዩ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ተፈናቅለው በባሕር ዳር ከተማ በችግር ውስጥ ይገኛሉ። ከድጋፉ ባለፈ በአቅማቸው የሚሠሩት ሥራ ቢመቻች ራሳቸውን ማሥተዳደር እንደሚችሉም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራ ሕዝብ ለዓመታት ሲያነሳቸው የነበሩ አጀንዳዎችን ማንሳታቸውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ተሳታፊዎች ተናገሩ።
Next article“የአሚኮ የግቢ ልማት ለሌሎች ማስተማሪያ የሚኾን ነው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)