የአማራ ሕዝብ ለዓመታት ሲያነሳቸው የነበሩ አጀንዳዎችን ማንሳታቸውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

20

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መጋቢት 27/2017ዓ.ም የተጀመረው የአማራ ክልል የጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ እንደቀጠለ ነው። በመጀመሪያ ዙር የተሳተፉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለቀናት አጀንዳቸውን ሲያሰባስቡ ሰንብተዋል። አጀንዳቸውን አጠናቅረው በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚሳተፉ ተሳታፊዎችም ተመርጠዋል።

የተመረጡት ተሳታፊዎችም በቆይታቸው “ሀገር እና ሕዝብን ይጠቅማል ያልነውን አጀንዳ ነቅሰን አውጥተናል” ነው ያሉት። ከሰሜን ሸዋ ዞን ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ እንደተመረጡ የነገሩን አባት ሀገራዊ ምክክር ከጅምሩ መልካም ሥንቅ ሰንቀንበታል ብለዋል። ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ሰላም እንድትሄድ፣ አንድነት እንዲጠናከር፣ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተው በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ሠርተው እንዲኖሩ ምክክር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በቆይታቸው ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅም አጀንዳ መምረጣቸውንም ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ አሉኝ የሚላቸውን እና ለዓመታት ሲያነሳቸው የነበሩ አጀንዳዎችን አንስተናል ነው ያሉት። ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ነጥቦች ትኩረት እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በሰላም፣ በአንድነት እና በፍቅር እንዲኖሩ ሀገራዊ ምክክር ወሳኝ ጉዳይ መኾኑን ነው የተናገሩት። የመረጧቸው አጀንዳዎች የአማራ ሕዝብ ጥቅሞችን አስከብረው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በእኩልነት የሚያኖሩ መኾናቸውን ነው የገለጹት።

የአማራ ክልልን ወክለው በሀገራዊ ምክክር ሲሳተፉም ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። እኛ ከመረጥናቸው አጀንዳዎች በተጨማሪ ሌሎች የሚመርጧቸው አጀንዳዎች ደግሞ ተጨማሪ ጉልበት ይኾናሉ ነው ያሉት። ምሁራን የተመረጡ አጀንዳዎችን በመምረጥ በኩል ትልቅ አደራ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተፈናቃዮችን ወክለው እንደመጡ የነገሩን ተሳታፊ አጀንዳዎችን በነጻነት እና በገለልተኝነት መምረጣቸውን አንስተዋል። ሀገራዊ ምክክሩ የመፈናቀል ችግርን እና ሌሎች የኢትዮጵያ ችግሮችን ይፈታል ብለን ትልቅ ተስፋ አድርገንበታል ነው ያሉት።

በምክክር አንድነታችንን አጠናክረን በአንዲት ሀገር በደስታ መኖር እንችላለን ብለዋል። የሀገር አንድነትን በማጠናከር ሰላምን ለማጽናት ምክክር ወሳኝ መኾኑንን ገልጸዋል።

የመረጧቸው አጀንዳዎችም አንድነትን የሚያጠናክሩ ሕዝብ በሰላም እንዲኖር የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንደተመረጡ የነገሩን ተወካይም ለቀናት ባደረግነው የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደት በርካታ አጀንዳዎችን ለይተናል ነው ያሉት። የተሳታፊዎች ምርጫ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ አሳታፊ እና አካታች መኾኑን ገልጸዋል።

በሀገራዊ ምክክር በሚኖራቸው ተሳትፎም ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል። የተሠራው ሥራ ታሪካዊ መኾኑንም ገልጸዋል።

አንድም የክልሉ አጀንዳ እንዳይቀር ጥረት አድርገናል፣ በስፋትም ተወያይተናል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ችግር መፍቻ መንገድ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነው ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄዎች የሚፈቱትም በምክክር መኾኑን ነው የገለጹት።

ከደቡብ ወሎ ዞን እንደተመረጡ የነገሩን ሌላኛዋ ተወካይ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የሕዝብን ጥያቄ የለየ፣ የሁሉም ሀሳብ ያካተተ ነው ብለዋል። አጀንዳ አለኝ የሚል ሰው ሁሉ አጀንዳውን ማቅረቡንም ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክር ነጻ እና ገለልተኛ መኾኑንም ገልጸዋል። መፈታት አለባቸው ያሏቸውን ጥያቄዎች ማንሳታቸውንም ተናግረዋል። በቀጣይ በሚኖረው ሥራም በንቃት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዘላቂ ሰላምን በማምጣት ረገድ የባሕል ፍርድ ቤቶች ሚና ከፍተኛ መኾኑን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ገለጹ።
Next articleየአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን እገዛ ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ።