
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና እውቅና ለመስጠት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 298/2017 ዓ.ም ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እና ወጭ ቆጣቢ የፍትሕ አገልግሎትን በመስጠት ረገድ የባሕል ፍርድ ቤቶች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሁሉንም ማኅበረሰብ በመደበኛው የፍርድ አገልግሎት ብቻ መሸፈን አዳጋች ሊኾን ስለሚችል ሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓቶችን መልክ በመስጠት እና በሕግ አግባብ በመደገፍ መጠቀም ተገቢ እንደኾነም ገልጸዋል። የባሕል ፍርድ ቤቶችን የመጠቀም ባሕሉም ሌሎች ሀገሮችም የሚጠቀሙበት አዋጭ መንገድ ነውም ብለዋል።
የአማራ ክልል ማኅበረሰብ በርካታ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን የሚጠቀም በመኾኑ ይህን መሠረታዊ ነገር በሕግ መደገፍም ተገቢ እንደኾነ ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት። ይህ ተግባር ታች ድረስ ወርዶ ተግባራዊ ይኾን ዘንድ በቀጣይ በርካታ ተግባራት እንደሚከወኑም ተናግረዋል። የባሕል ፍርድ ቤቶች ባሕልን እና እሴትን በጠበቀ መንገድ የግጭት መፍቻ ዘዴ ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም በየደረጃው ያለው የመንግሥት አካል ተገቢ ድጋፍ እንዲሰጥም ይደረጋል ነው ያሉት።
የባሕል ፍርድ ቤቶችን በተገቢው መንገድ ማገዝ እና መደገፍ ከተቻለ “ዘላቂ ሰላምን በማምጣት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫዎታል” ነው ያሉት። በውይይቱ ላይ የተሳተፉት እና ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የመጡት ነጋ እውነቴ (ዶ.ር) በሕዝቦች ዘንድ ቅቡልነት ያለው የሽምግልና ሥርዓትን በሕግ አግባብ ዕውቅና መስጠት እና መደገፍ መቻሉ ተገቢ ነው ብለዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የሰላም ለሁሉም የበጎ አድራጎት ማኅበር ፕሬዝዳንት አብርሃም አያሌው ናቸው። የባሕል ፍርድ ቤት መቋቋሙ ፍትሕን ከማስፈን በዘለለ ባሕልን እና ወግን ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር ሚናው ከፍተኛ እንደኾነ ተናግረዋል። ይሁን እና ለተፈጻሚነቱ ሁሉም አካል ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባም አስተያየት ሰጭዎቹ ጠቁመዋል።
በእውነትም የባሕል ፍርድ ቤቱ ውጤታማ ይኾን ዘንድ እና የማኅበረሰቡ የፍትሕ ምንጭ እንዲኾን የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ ሊኾን እንደሚገባ በውይይቱ በአጽንኦት ተነስቷል። የወጣውን አዋጅ ወደ ተግባር ለማስገባት እና ተግባራዊ ለማድረግ በቀጣይ ዝርዝር መመሪያዎች እንደሚወጡም ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
