በአማራ ክልል የሚካሄደው ሁለተኛው ምዕራፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ተጀመረ።

29

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የሚያካሂደው አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ የመጀመሪያው ዙር መጋቢት 27/2017 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል። በዚህ ዙር ከየአካባቢው የተወከሉ የኅብረተሰብ ተወካዮች አጀንዳዎችን አቅርበው በመወያየት አጠናቅረዋል።

ዛሬ ደግሞ ሁለተኛው ዙር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ቀጥሏል። በዚህ ዙር ደግሞ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና ባለድርሻ አካላት ይሳተፉበታል። እነዚህ አካላት ከተለያዩ አካባቢዎች ተጉዘው በባሕር ዳር ከተማ በመገኘት በቀጣዮቹ ቀናት በሚኖራቸው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎች ዙሪያ የቅድመ ዝግጅት ውይይቶችን እያደረጉ ነው።

ከቅድመ ውይይት በኋላም ለቀናት በሚኖራቸው ቆይታ አጀንዳዎቻቸውን በማቅረብ ሰፊ ምክክር ያደርጋሉ፤ በአንድ ላይ አጠናቅረውም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ያስረክባሉ።

በቅድመ ውይይቱ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም “ሀገር በምክክር ትጸናለች ብላችሁ በማመን በሂደቱ ለምትሳተፉ ሁሉ ሀገር ታመሰግናችኋለች” ብለዋል። መሠረታዊ ጉዳዮችን ለይቶ በመቅረጽ ለሀገራዊ ምክክር ማቅረብ ከሁሉም ተሳታፊዎች እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።

ከምሁራን እና ከታላላቅ ሰዎች ብዙ ሀገራዊ አበርክቶ እንደሚጠበቅ የገለጹት ኮሚሽነሩ ለሀገር መፍትሔ የሚኾኑ አጀንዳዎችን በማሰባሰቡ በኩል ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑም አስገንዝበዋል።

ከቤተሰብ ጀምሮ ሰዎች ብዙ ጉዳዮች አሉባቸው፤ ለሀገራዊ ምክክር መቅረብ ያለባቸው ግን ዋና ዋናዎቹ እና እንደሀገር በሰላም ለመኖር እና ለአብሮነት ፈተና የኾኑ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሌላው ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) ኮሚሽኑ ምሁራን እና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የምክክሩ ዋነኛ ተሳታፊ እንዲኾኑ፣ ለሀገራዊ ችግሮችም ሁነኛ የመፍትሔ ሀሳቦችን እንዲያመነጩ እየተሠራ ነው ብለዋል።

“ምክክር እውነትን የመፈለግ ሂደት ነው” ያሉት ዶክተር ዮናስ በውስጡም መደማመጥ፣ መግባባት እና መከባበር ሊኖርበት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። ምክክር ሁሉም አሸናፊ ኾኖ የሚወጣበት ሰላማዊ አውድ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

በሕዝብ እና በሕዝብ መካከል፣ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል መተማመን እና ለአንዲት ሀገር ልዕልና በጋራ እና በመተማመን ለመሥራት መመካከር እና መፈቃቀር ፍቱን መድኃኒት ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ።

በመኾኑም ምሁራን እና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ንቁ ተሳታፊ በመኾን የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፍ በዛሬ ውሎው የማኅበረሰብ ተወካዮች ምርጫ እና የአጀንዳዎችን የማጠናቀር ሥራ ተከናውኗል።
Next articleየፈተና ውጤት ማሳወቅ