የአማራ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፍ በዛሬ ውሎው የማኅበረሰብ ተወካዮች ምርጫ እና የአጀንዳዎችን የማጠናቀር ሥራ ተከናውኗል።

29

ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ የአማራ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፍ የአራተኛ ቀን ውሎውን አስመልክተው ለአሚኮ መግለጫ ሰጥተዋል። ቃል አቀባዩ እንዳሉት በዛሬ ውሎው ሁለት አበይት ተግባራት ተከናውነዋል።

በጠዋቱ ክፈለ ጊዜ ክልሉን በመወከል በመጨረሻው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ እና የክልሉን አጀንዳ የሚያጠናቅሩ 270 ተወካዮች የተመረጡበት ነበር። የተወካዮች ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና በሕዝብ ፊት በካርድ የተከናወነ ነበር። በቅድሚያ 1 ሺህ ዕጩዎች ቀርበው ከዚህም ውስጥ 270ዎቹ በካርድ የተመረጡ ናቸው ብለዋል ቃል አቀባዩ።

እነዚህ ተወካዮች በክልሉ ለሁለተኛ ዙር በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ላይም እንደሚሳተፉ አቶ ጥበቡ ገልጸዋል። በዛሬው ውሎ የተከናወነው ሌላው ተግባር የተነሱ አጀንዳዎችን የማጠናቀር ሥራ ነው። ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የመጡ የማኅበረሰብ ወኪሎች በቡድን ተከፋፍለው የተለያዩ አጀንዳዎችን ሲያነሱ ሰንብተዋል።

ዛሬ ደግሞ በጋራ በመሰባሰብ ከየቡድኑ የተነሱ አጀንዳዎችን በአንድ የማጠናቀር እና የመሰነድ ተግባር እየተከናወነ ነው። መርሐ ግብሩ በነገው ዕለት የሚቀጥል ሲኾን በመጀመሪያው ዙር የተነሱ አጀንዳዎችን የማጠናቀር ሥራ ይጠናቀቃል። ሚያዚያ 02/2017 ዓ.ም ደግሞ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሁለተኛው ዙር የአጀንዳ ልየታ ይጀመራል።

በዚህ ዙርም የሚነሱ አጀንዳዎች ይሰነዳሉ፤ በማጠቃለያው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ተጨማሪ ሰዎችም ይለያሉ ብለዋል ቃል አቀባዩ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየመንግሥት ሠራተኛው ዶሮ በማርባት ኑሮውን እንዲደጉም እየተሠራ ነው።
Next articleበአማራ ክልል የሚካሄደው ሁለተኛው ምዕራፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ተጀመረ።