የመንግሥት ሠራተኛው ዶሮ በማርባት ኑሮውን እንዲደጉም እየተሠራ ነው።

41

ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2017 (አሚኮ) የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ጽሕፈት የመንግሥት ሠራተኛውን በዶሮ ሀብት ልማት ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለማድረግ ሥልጠና ሰጥቷል። የጽሕፈት ቤቱ የእንስሳት ርባታ ተዋጽኦ እና መኖ ልማት ዳይሬክተር መኳንንት ዳምጤ እንዳሉት በክልሉ የአመጋገብ ሥርዓትን ለማስተካከል እና የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ እየተሠራ ይገኛል።

የኑሮ ውድነት ተጋላጭ ከኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የመንግሥት ሠራተኛው አንዱ ነው። የመንግሥት ሠራተኛው ያለውን እውቀት ተጠቅሞ በጎጆ ርባታ (የኬጅ ሥርዓት) ዶሮ በማርባት እንዲጠቀም ማድረግ አንዱ አማራጭ መኾኑን ገልጸዋል። የጎጆ ዶሮ ርባታ በትንሽ ቦታ እና በውስን ሀብት ዶሮን በማርባት የቤተሰብ አመጋገብ ሥርዓትን ከማስተካከል ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ሀብት ማፍራት የሚያስችል ነው።

በአንድ ካሬ ላይ በተሠራ ባለሁለት ወለል የጎጆ ርባታ ቦታ እስከ 20 ዶሮዎችን ማርባት እንደሚቻል በማሳያነት አንስተዋል። በአንድ ካሬ ላይ ባረፈ ባለሁለት ወለል የጎጆ የርባታ ቦታ እስከ 20 ዶሮዎችን ማርባት ከተቻለ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ባለው የመኖሪያ ግቢ ውስጥ ባለው ቦታ የካሬ እና የወለሉን (ፎቁን) መጠን በመጨመር ምን ያህል ዶሮዎችን ማርባት እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም።

አሠራሩ ብዙ የሰው ኃይል የማይፈልግ እና መኖ ቆጣቢ ጭምር በመኾኑ ለመንግሥት ሠራተኛው አቅም ይኾናል ብለዋል። ከዚህ በፊትም የጎጆ ርባታ (የኬጅ ሥርዓት ) የተሠማሩ የመንግሥት ሠራተኞች ከራሳቸው አልፎ ለገበያም እያቀረቡ የሚገኙ መኖራቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም ወደ ርባታ ለማስገባት በባሕር ዳር ለሚገኙ ለተወሰኑ ተቋማት ሠራተኞች ሥልጠና መሥጠት አሥፈልጓል ብለዋል።

ወደ ሥራ ለሚገቡ የመንግሥት ሠራተኞች በባሕር ከተማ ከሚገኙ አርቢዎች ቄብ ዶሮዎችን ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል። የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ እንደመጡ የነገሩን አብራራው ዳኘው እንዳሉት የተሠጠው ሥልጠና የመንግሥት ሠራተኛ ባለው ቦታ እና ትርፍ ጊዜ ተጨማሪ የሥራ እድል የሚፈጥር ነው።

ሥራው ተጨማሪ ሀብት ለማፍራት እና የአመጋገብ ሥርዓትን ለማስተካከል የሚያስችል በመኾኑ በቀጣይ ወደ ርባታ እንደሚገቡ ነው የገለጹት። ሌላኛው የሥልጠናው ተሳታፊ አቶ ማስተዋል አያልነህ ናቸው። አቶ ማስተዋል ከዚህ በፊት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የግብርና ባለሙያ ኾነው ለስድስት ዓመት ያህል አገልግለዋል።

ይሁን እንጅ በተለያዩ ምክንያቶች የመንግሥት ሥራውን በመልቀቅ በ1 ሺህ 200 የአንድ ቀን ጫጩት ወደ ርባታ እንደገቡ ነው የነገሩን። ከ10 ዓመት በላይም በሥራው ላይ ይገኛሉ። በዓመትም ከ70 ሺህ በላይ ቄብ ዶሮዎችን ለማኅበረሰቡ እያሠራጩ ይገኛሉ። እስከ 25 ለሚኾኑ ዜጎችም በጊዜያዊነት እና በቋሚነት የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል።

በዶሮ ርባታ ባገኙት ሀብት ባለሦስት ወለል መኖሪያ ቤት ገንብተዋል። በቀጣይም ሥራውን ለማስፋት ፕሮጀክት አዘጋጅተው ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። የዶሮ ርባታ በትንሽ ቦታ እና ውስን ሀብት በመሥራት የተመጣጠነ ምግብ ከመመገብ ባለፈ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የሚያስችል ሥራ በመኾኑ የመንግሥት ሠራተኛው

በመኖሪያ ቦታው አርብቶ መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበፈጠራ ውጤቶች ላይ ያተኮረ ውድድር በጎንደር ከተማ ተካሄደ።
Next articleየአማራ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፍ በዛሬ ውሎው የማኅበረሰብ ተወካዮች ምርጫ እና የአጀንዳዎችን የማጠናቀር ሥራ ተከናውኗል።