
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እየገጠመው ያለውን ጂኦ-ፖለቲካል ውጥረት ለመፍታት የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ በተመለከተ አብመድ ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማት አቶ ዘሪሁን አበበ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
እንደዲፕሎማቱ ማብራሪያ ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እየተተገበሩ ያሉ መሠረታዊ መርሆዎችን መሠረት አድርጋ ግድቧን እየሠራች አሁን ካለበት የግንባታ ደረጃ ደርሳለች፡፡ ከድህነት ለመውጣት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየገነባች መሆኗን ለዓለም ሕዝብ ስታሳውቅ ቆይታለች፤ አሁንም ማሳወቋን ቀጥላለች፡፡
እስካሁን በነበሩት ሂደቶች ግድቡ እውን እንዳይሆን የተለያዩ ጫናዎች ከየአቅጣጫው ሲሰነዘሩ እንደነበርም ዲፕሎማቱ ጠቅሰዋል፡፡ ጫናዎቹ የግድቡን ግንባታ ለአፍታም እንዲቆም አላደረጉትም፤ ይህ የሀገሪቱን የስኬት ጉዞ የሚያሳይ ትልቅ ድል መሆኑን በመጥቀስ፡፡ “ውጤቱ ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም፤ በአንድም በሌላ መልኩ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እየተከተለች ያለችው የዲፕሎማሲ ስልት ያስገኘው ነው” ብለዋል አቶ ዘሪሁን አበበ፡፡
እንደዲፕሎማቱ ገለጻ ኢትዮጵያ ቸርም ስለሆነች፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋም በመጠቃቀም ላይ የተመሠረተ በመሆኑ “ብቻየን ልልማ” አላለችም፡፡ ከታችኞቹ ሀገራት ጋር በጋራ ለመልማት አማራጭ አስቀምጣለች፡፡ ግብፅ ይህን አላደረገችውም፡፡ የዓባይን ወንዝ ተጠቅማ እስከዛሬ በገነባቻቸው ግድቦች በረሃዋን ወደ ገነት ስትቀይር በድህነት ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያን አላማከረቻትም፡፡ ይህን የዓለም ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል፤ እንዲያውቅም ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
በመሠረቱ በዓለም ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ያላቸው ሀገራት እየተከተሉት ካለው ስልት አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያ ለጋራ ተጠቃሚነት እያሳየች ያለችው የዲፕሎማቲክ ግንኙነት የተሻለ ነው፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ያላቸው አብዛኞቹ ሀገራት የየራሳቸውን የቤት ሥራ ነው የሚሠሩት፡፡ ኢትዮጵያ ግን የግድቡን የጥናት ሰነዶች ሁሉ በማጋራት ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር እየሠራች መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አቤቱታ የሚያቀርቡ ሀገራት ኃላፊነት የተሞላበት የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ አሠራር ማሳያ አድርገው ሊውስዱት እንደሚገባም አቶ ዘሪሁን አበበ ጠቅሰዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ‘ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ያለው ሀገር ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ይጠቀም፤ በሌላውም ላይ ጉልህ ጉዳት አያድርስ’ በሚለው የዓለም ልማዳዊ ሕግ መሠረትም ነው ግድቡን እየገነባች የምትገኘው፡፡ በጀመረችው አግባብም ሀብቷን መጠቀም ትቀጥላለች፤ ሀቁ ይህ ነው” ብለዋል አቶ ዘሪሁን፡፡
በራሷ አቅም፣ ያለማንም የገንዘብ ድጋፍ እየገነባች ያለችውን ግድብ አስመልክቶ ከሁለቱ የግርጌ ተፋሰስ ሀገራት መተማመንን ለማጎልበት ረዥም ርቀት መሄዷንም ጠቅሰዋል፡፡ “በወርኃ መጋቢት 2007 ዓ.ም ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በመሪዎች ደረጃ በሱዳን ያካሄዱት የጋራ የመሪዎች መግለጫ ስምምነት የጥረቱ ማሳያ ነው፡፡ ስምምነቱን ሁለቱም ሀገራት አውቀውት፣ ጉዳዩን አምነውበት የተካሄደ በመሆኑ የግንባታውን ቀጣይነት ሊያከብሩት ይገባል፡፡ አምነውም ገብተውበታል፡፡ ግንባታ ኮንክሪት መደርደር ብቻ ሳይሆን ሙሌቱንም እንደሚጨምር መረዳት ደግሞ ተገቢ ነው” ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ዘሪሁን ገለጻ የኢትዮጵያ በመጠቃቀም ላይ በተመሠረተ የግንኙነት መርህ፣ ማንም ሳይጎዳ በራስ ሀብት የራስን ችግር ለመቅረፍ እየተደረገ ያለው የዲፕሎማሲ አካሄድ ትክክለኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በራሷ ግዛት፣ የራሷን ውኃ፣ ለዚያውም ለታችኞቹ ሀገራት ተመልሶ ጥቅም የሚሰጥ የኃይል ማመንጫ ግድብ “አትሞይም” የሚላት ሕግ የለም፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በመጭዎቹ የክረምት ወራትም የመጀመሪያውን ዙር የግድቡን የውኃ ሙሌት እንደሚጀምር አሳውቋል፡፡ የግድቡ ግንባታ ሂደት እስከቀጠለ ድረስ የውኃው ተፈጥሮሯዊ ሂደት በመጭው ሐምሌ ግድቡ በውኃ መሞላቱም አይቀሬ ነው፡፡
ዓለም ተገልብጦ ከኢ-ፍታዊነት ጋር እስካልቆመ ድረስ ለኢትዮጵያ ስጋት ነው የሚባል ነገር እንደሌለም አቶ ዘሪሁን ጠቅሰዋል፡፡ “የሚያጋጥሙ ችግሮችም ቢኖሩ ባሉት የሕግ ማዕቀፎች ሁሉም እየተፈቱ መሄዳቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ኢትዮጵያም የዓባይን ውኃ በፍትሐዊነት መጠቀሟን ትቀጥላለች” ሲሉ የቀጣይ አቅጣጫዎችን ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡