
ጎንደር: መጋቢት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፈጠራ ውጤቶች የማኅበረሰብን ችግሮች በመፍታት፣ ኑሮን በማቅለል እና ከውጭ የሚገቡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመተካት ለሀገር ልማት እና እድገት የላቀ ጠቀሜታ እንዳላቸው የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ተስፋሁን መኮንን ገልጸዋል።
የተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች የእውቀት ሽግግርን ለማስፋት የጎላ ሚና እንዳላቸውም አስረድተዋል። በውድድሩ በጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ስር የሚገኙ ክላስተር ኮሌጆችን ጨምሮ ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ ኾነዋል። ችግርን ወደ ሀብት በመቀየር በኢንተርፕራይዞች እና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን ያነሱት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ዘርፋን ለማሳደግ የከተማ አሥተዳደሩ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በዕለቱ የፈጠራ ሥራውን ያቀረበው ዳንኤል መንግሥቴ እንደተናገረው የፈጠራ ውጤቶች በማኅበረሰቡ የሚነሱ ችግሮችን የሚፈቱ መኾናቸውን ገልጿል። ያቀረበው የፈጠራ ውጤት የውጭ ምንዛሬን የሚያስቀር መኾኑን የገለጸው ደግሞ ውብሸት ታዬ ነው። በውድድሩ አንደኛ የሚወጣው የፈጠራ ውጤት በኮምቦልቻ ከተማ በሚደረገው ክልል አቀፍ ወድድር ላይ እንደሚሳተፍ ተገልጿል።
ዘጋቢ:- ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን