
ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሁሉ ነገር በልኩ ይኾን ዘንድ ሕጎች መሠረታዊ ነገሮች ናቸው። የሕግ የበላይነት ሲሰፍን የአንድ ሀገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መልካም ይኾናሉ።
ሕግ በሌለበት እና ባልተከበረበት ኹኔታ ደግሞ ሥርዓት አልበኝነት ሥር ይሰዳል፤ የሀገር ሰላምም ይናወጣል። እኩልነት እና ፍትሐዊነትም በዘፈቀደ ይኾናል። ለዚህ ሁሉ ታድያ ሕግ የማይናወጥ ሚዛን ኾኖ ያገለግላል። የዛሬው የሕጉ ምን ይላል አጀንዳችንም የገጠር መሬት የውርስ ሕጉን በጨረፍታ ይተነትናል።
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ላይ እንደተደነገገው አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ከመንግሥት መሬትን በነጻ የማግኘት መብት አላቸው ይላል፡፡ የመሬት የባለቤትነት መብትም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሲኾኑ ዜጎች በመሬቱ ላይ ላፈሩት ንብረት የባለቤትነት መብት አላቸው ሲል ሕጉ ያስቀምጣል፡፡
አቶ አብዬ ካሳሁን የአሚኮ የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር ናቸው። የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 456/1997 ማውጣቱን ተከትሎ የአማራ ክልልም ከዚያ የተቀዳ የተለያዩ አዋጆችን በማውጣት ሲተገብር ቆይቷል ይላሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የገጠር መሬት አጠቃቀም እና አሥተዳደር አዋጅ ቁጥር 252/2009 በአብነት ይጠቀሳል ብለዋል፡፡
በፌዴራል ደረጃ ደግሞ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1324/2016 አስቀድሞ የነበረውን በአዋጅ ቁጥር 456/1997ን ተክቶ እንደታወጀም ተናግረዋል፡፡ የአርሶ እና የአርብቶ አደሮችን የመሬት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ሀገራችን በዓለም አቀፍ እንዲኹም በአህጉር አቀፍ የገባችውን ግዴታ ተፈጻሚ ለማድረግ፣ የተሟላ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ መሬትን በዕቅድ እና በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲኹም የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማጠናከር የታወጀው የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1324/2016 ስለ ውርስ በሚደነግገው አንቀጽ 12 ሥር የተቀመጠ ነው ባይ ናቸው።
የገጠር መሬት ባለይዞታ በፍትሐ ብሔር ሕጉ የውርስ ድንጋጌዎች መሠረት ለማንኛውም ሰው ማውረስ ይችላል በማለት ደንግጓል ነው ያሉት አቶ አብዬ፡፡ የገጠር መሬትን በኑዛዜ ወይም ያለ ኑዛዜ ውርስ በሚመራባቸው የፍትሐ ብሔር ሕጎች መሠረት ማውረስም መውረስም እንደሚቻል ሕጉ ላይ ተቀምጧል ብለዋል፡፡
የኑዛዜ ወራሽነት ሕጉ የሚጠይቀውን መስፈርት በማሟላት የሚፈጸም ነው። ባለይዞታው በኑዛዜ ሳያወርስ በሞተ ጊዜ ወይም ኑዛዜው ፈራሽ ከኾነ በሕጉ የተመለከቱት ያለኑዛዜ የውርስ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ እንደሚኾንም 1324/2016 አንቀጽ 12 (2) በግልጽ ተቀምጧል ብለዋል።
የተሻሻለው የመሬት ሕግ በአማራ ክልል የገጠር መሬት አሥተዳደር ሕጎች በተመለከተ የቀድሞው ሕግ ማለትም 133/1998 ለቤተሰብ አባል ማውረስ እንደሚቻል ይደነግግ ነበር፡፡ ይህ ሕግ ግን በርካታ ችግሮችን እያስነሳ በመቆየቱ በማሻሻል አዋጅ ቁጥር 252/2009 ዓ.ም ተሻሽሎ እንደወጣ አስረድተዋል።
ይህ የተሻሻለው የመሬት ሕግ ደግሞ ውርሱ በኑዛዜ ከኾነ እና በግብርና ሥራ ለሚተዳደር ወይም ለመተዳደር ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው (ከፍተኛ የመሬት መጠኑን ሳያልፍ) ማውረስ እንደሚቻል ሕጉ አስቀምጧል ነው ያሉት፡፡ ያለኑዛዜ ደግሞ ልጅ፣ ወላጅ እንዲኹም በሕግ የተፈቀደ የቤተሰብ አባል መውረስ ይችላልም ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
አዲሱ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ የመሬት ውርስ ጉዳይ በፍትሐ ብሔር ሕጉ የውርስ ድንጋጌዎች መሠረት የሚመራ መኾኑን ደንግጓል፤ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 826 ጀምሮ ስለ ውርስ በርካታ ድንጋጌዎችን በግልጽ አስቀምጧል ነው ያሉት፡፡ ይሁንና ይላሉ ዳይሬክተሩ ወራሾች ወራሽ በመኾናቸው ብቻ መሬቱን እኩል የመካፈል መብት አይኖራቸውም ብለዋል፡፡
ውርሱ የሚከናወነው ወራሾች ከውርስ በፊት ያላቸውን ይዞታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲኾን ይህም የመሬትን ተጠቃሚዎች በፍትሐዊነት እንዲጠቀሙ ለማስቻል ታስቦ የተደነገገ ነው ብለዋል፡፡ ይህም በግለሰብ ደረጃ የተፈቀደውን የመሬት ጣሪያ ግምት ውስጥ በማስገባት ሊኾን እንደሚችል ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት ወራሾች እኩል የመውረስ መብት ያላቸው ስለነበር አራት ሄክታር መሬት የነበረው እና አንድ ሄክታር መሬት የነበረው ሰው እኩል ይወርሱ እንደነበር አውስተዋል፡፡ ይህን ለማስወገድ ሕጉ መፍትሔ አስቀምጧል ነው ያሉት፡፡ ውርስ በፍትሐ ብሔር ሕጉ መሠረት እንዲከናወን የተደረገበት ዋናው ምክንያት የቤተሰብ አባል በሚል በተሻረው ሕግ የተቀመጠው ለትርጉም የተጋለጠ እና አሻሚ ስለኾነ እንደኾነም አቶ አብዬ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ባለይዞታዎች መሬታቸውን የቤተሰብ አባል የሚባሉት እንደሚወርሷቸው ስለሚያውቁ መሬቱን ልጆቻችን የማይወርሱት ከኾነ በሚል በመሬቱ ላይ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ አለመሥራት፣ በመሬቱ ላይ ያሉ ዛፎችን እየቆረጡ በመሸጥ ለአካባቢ ውድመት ምክንያት እየኾነ እና አንዳንድ ጊዜም መሬቱን ሊወርስ የሚችል ልጅ እንዳይማር በማድረግ ጭምርም የሚገለጽ ነው ብለዋል፡፡
በሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን