
ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የሚያካሂደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ አራተኛ ቀኑን ይዟል። በዛሬው የውሎ መርሐ ግብር የኅብረተሰብ ክፍል ተሳታፊዎችን የሚወክሉ ሰዎች ምርጫ እየተካሄደ ነው። ሂደቱን በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ካደረጉት ተሳታፊዎች መካከል አቶ በሪሁን ይመር በምክክር ሂደቱ መሳተፍ ከጀምሩበት ቀን አንስቶ ለሀገር የሚበጁ ሀሳቦችን ሲያዋጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የሚስተዋሉ ችግሮች በውይይት እና ምክክር ተቀርፈው ሰላም እንደሚሰፍን ተስፋ ይዘው በክልላዊ የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፉ እየተሳተፉ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ዛሬ በአጀንዳ ልየታው አራተኛ ቀን ውሎ በዋናው ሀገራዊ ምክክር ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን እንደመረጡም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሻለ የውይይት እና የምክክር ልምድን ይዞ የመጣ፣ ለተሻለ የዴሞክራሲያዊ ልምምድም የሚጋብዝም ነው ብለዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ እጩ ተወካዮች በጥቆማ መመረጣቸውንም ተናግረዋል። እጩዎች ራሳቸውን እና ሀሳባቸውን በመድረኩ ካስተዋወቁ በኋላ የመጨረሻ ተሳታፊዎች ደግሞ በካርድ እንደሚመረጡ ነግረውናል። ምርጫው ፍጹም ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻ እና ገለልተኛ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
የተሳታፊዎች ልየታ የምርጫ ኮረጆ ባዶ መኾኑ ተረጋግጦ እና እያንዳንዱ የሕዝብ ወኪሎች የሚፈልጓቸውን ተሳታፊዎች ስም ጽፈው ወደ ኮረጆው መጨመራቸውንም ነግረውናል። በመጨረሻም ኮረጆው ተከፍቶ ድምጽ ሲቆጠር በመጨረሻው ሀገራዊ ምክክር ላይ ክልሉን ወክለው የሚሳተፉ ሰዎች ይለያሉ ነው ያሉን።
ሌላዋ ተሳታፊ ዓለምነሽ አባተ ለሀገር እና ለሕዝብ ሲሉ ከልጆቻቸው ተነጥለው እና የንግድ ሥራቸውን ዘግተው በምክክር ሂደቱ ላይ እንደተገኙ ተናግረዋል። የምክክር ሂደቱ በውጤታማነት ተጠናቅቆ የሀገር ችግሮች እንዲፈቱ በንቃት ከመሳተፍ በተጨማሪ የእናትነት ጸሎታቸውን ጭምር እያደረሱ መኾኑንም ነግረውናል።
የምክክሩ ሂደት ነጻ እና ከየትኛውም አይነት ጫና የጸዳ መኾኑን ጠቁመዋል። በመጭው ሀገራዊ ምክክር ላይ የሚሳተፉ አካላት ሲመረጡም ዴሞክራሲያዊ፣ አካታች፣ እና ነጻ ኾነው ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን