
ከሚሴ: መጋቢት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የማኀበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን የቁርጥ ክፍያ እና ዞናዊ ከፍ ያለ ቋት ምስረታን መሠረት ያደረገ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ወርቁን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች፣ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ መሪዎች እንዲኹም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና የወረዳዎች የጤና መድኅን ቦርድ አባላት ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ከዚህ በፊት የነበረው የወረዳ ቋት ከፍ ወዳለ ዞናዊ ቋት መመስረቱ ወረዳዎች እንዲደጋገፉ ከማድረጉ ባሻገር ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት በጤና ተቋማት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ኡስማን አሊ ከፍ ያለ ቋት ምስረታው በጤና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለጤና መድኅን ተጠቃሚዎች የመድኃኒት አቅርቦት ለመስጠት ያግዛል ነው ያሉት።
ከዚህ በፊት የጤና ተቋማት ለጤና መድኅን ተጠቃሚዎች ለሰጡት አገልግሎት ተቋማት በወቅቱ እንደማይከፈላቸው ጠቅሰው አሁን ላይ ከፍ ያለ ቋት መመሥረቱ ለጤና ተቋማት በተጠቃሚዎቹ ልክ የቅድመ ክፍያ ሥርዓት እንዲዘረጋላቸው መደላድል መፍጠሩን አሥረድተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሕመድ ሁሴን በከተማ እና በገጠር ያሉ የጤና መድኅን ተጠቃሚዎች የሚያነሱትን ቅሬታዎች በመቅረፍ ቀልጣፋ እና ምቹ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ወርቁ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት በሀገር ደረጃ በ1 ሺህ 100 በላይ ወረዳዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ለጤና መድኅን ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት ለማቅረብ በተሠራው ሥራ ከ470 በላይ የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤቶችን በወረዳዎች በመክፈት በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው እንዲያቀርቡ እየተደረገ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የተጀመረው ዞናዊ ከፍ ያለ ቋት ምስረታም በ30 ዞኖች የተጀመረ መኾኑን ገልጸው በቀጣይ በኹሉም አካባቢዎች ለማስፋፋት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን