
ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በቀጣይ ወራት የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ዙሪያ እየተወያዩ ነው። በውይይቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በዓመቱ የታቀዱ በርካታ ተግባራት መኖራቸውን ገልጸዋል። ተቋማትን ለሚቀጥለው ጊዜ የማዘጋጀት እና የአሥፈጻሚ አካላት ሪፎርም ማድረግ አንደኛው ሥራ መኾኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ አሥፈጻሚው አካል የሚመራበት የ25 ዓመታት ዕቅድ መታቀዱንም ገልጸዋል።
የ25 ዓመቱ ዕቅዱ የረጅም እና የመካከለኛ ጊዜ ተልዕኮዎችን ግልጽ ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል። የአሥፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ምን መኾን መቻል አለበት የሚለው ጥናት መደረጉንም ገልጸዋል። የፍትሕ አካላትን የሚያቀናጅ፣ የክልሉን ሕዝብ የፍትሕ ጥማት ለማርካት የሚያስችል ሪፎርም እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም የነበረውን ሊያስቀር የሚችል እና የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል መኾኑንም አንስተዋል።
የጸጥታ አካላት ሪፎርም ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የጸጥታ ኀይል ሪፎርም ብዙ ጊዜ የወሰደ እና በትኩረት እየተሠራ ያለ መኾኑን ነው የገለጹት። የጸጥታ ኀይሉ ሪፎርሙ በውስጥ ያለውን አቅም እና ሊመጣ የሚችለውን ስጋት ታሳቢ ያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል። የልማት ድርጅቶች ሪፎርም እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። የልማት ድርጅቶች ለመንግሥት አቅም መኾን በሚችሉበት መንገድ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የልማት ድርጅቶች ተልዕኳቸውን በለየ መልኩ ሪፎርም መሥራት እንዳስፈለገ ነው ያነሱት።
የልማት ድርጅቶች በምን መልኩ መሥራት እንዳለባቸው ጥናት መጠናቱንም ገልጸዋል። የልማት ድርጅቶችን በቂ የንግድ ልምድ እና አቅም ያለው ሰው እንዲመራቸው ይደረጋል ነው ያሉት። የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በትኩረት ሊመራ የሚገባው ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል። በዓመቱ የማኅበራዊ፣ የምጣኔ ሃብታዊ፣ የፖለቲካዊ ልማት እና የሕግ ማስከበር ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት ዘርፉ እና በሌሎች ዘርፎች የተሻሉ ሥራዎችን ለመሥራት ተንቀሳቅሰናል ነው ያሉት። የተሻሉ ውጤቶችን ለመፈጸም ጥረት የተደረገበት እንደነበርም ገልጸዋል። “ቀጣይ ወራት በጥራት እና በፍጥነት ሥራዎችን የምናከናውንባቸው ጊዜያት ናቸው” ብለዋል። ሥራን በጥራት እና በፍጥነት ለማከናወን መሪን ማጥራት እንደሚጠበቅም አንስተዋል። የተሻለ ሥራ ለመሥራት መሪን ማጥራት በቀጣይም የሚተገበር መኾኑን ነው የተናገሩት። የመንግሥትን የመምራት አቅም ከፍ ማድረግ እና የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
በቀጣይ ጊዜያት ጠንካራ የፖለቲካ ሥራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። ባለፉት ጊዜያት በተሠራው ሥራ የተደናገረውን ኀይል የመመለስ እና ጽንፈኛ ኀይሉን ይደግፍ የነበረው እውነቱን እንዲረዳ መደረጉን ነው የገለጹት። ከዚህ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ሕዝብን ማወያየት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
አሁን ያለው ሁኔታ ለአማራ ሕዝብ የማይጠቅም መኾኑንም አመላክተዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ ተከታታይ ጉዳት የደረሰበት ሕዝብ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከዚህ በላይ እንዳይጎዳ ችግሩን መፍታት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ወደፊት የሚያራምድ እና አወንታዊ ለውጥ የሚያመጣ የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል። በልማት፣ በመልካም አሥተዳደር እና በሰላም ሥራዎች ላይ ውጤታማነትን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት። በተለይ በተመረጡ እና ልዩ ትኩረት በሚሰጣቸው ሥራዎች ላይ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በቀጣይ የሚሰጡ ተልዕኮዎችን በንቃት እና በብቃት መወጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን