ባለፉት ስድስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴው ግድብ 605 ሚሊዮን 523 ሺህ ብር ተሰብስቧል፡፡

242

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) በቦንድ ግዢ፣ በስጦታና በ“8100” የአጭር መልእክት ድጋፍ 605 ሚሊዮን 523 ሺህ ብር መሰብሰቡን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም ተናግረዋል፡፡ ከዲያስፖራ ቦንድ ሽያጭ ደግሞ ከ1 ሚሊዮን 38 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል፡፡

የግድቡ ምስል ያለበት “አሻራዬን አኑሪያለሁ” የሚል የደረት ባጅ (ፒን ባጅ) በመሸጥ ደግሞ 4 ሚሊዮን 600 ሺህ ብር በላይ መገኘቱን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ሕዝቡ ለሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ የሚያበረክተውን ድጋፍ እንዳልገደበውም ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም በመጋቢት የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን ወደ 49 ሚሊዮን ብር እንደሚጠጋ በማስታወስ ሚያዚያ ደግሞ ከ79 ሚሊዮን 459 ሺህ ብር በላይ መገኘቱ ድጋፉ እያደገ መሄዱን እንደሚያሳይ አቶ ኃይሉ አስገንዝበዋል፡፡

ነገር ግን ወረርሽኙ የቅስቀሳና ገቢ መሳባሰቢያ ዝግጅቶችና የሕዝብ ውይይት የሚካሄድባቸውን መድረኮች ለማሰናዳት እንቅፋት መፍጠሩን ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡

በአጠቃላይ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ በተለያዩ የድጋፍ ዓይነቶች የተሰበሰው ገንዘብ እስከ ሚያዚያ መጨረሻ ድረስ 13 ቢሊዮን 540 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ላይ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleዓባይ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ለደንበኞቹ የወለድ ቅናሽ አደረገ፡፡
Next article“ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ በፍትሐዊነት መጠቀሟን ትቀጥላለች፡፡” ዲፕሎማት ዘሪሁን አበበ