“በሀገር ደረጃ ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ለውጥ መጥቷል” ግርማ አመንቴ (ዶ.ር)

13

ደሴ: መጋቢት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ግብርና ሚኒስቴር ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ለቀበሌ ግብርና ባለሙያዎች የደረጃ ማሻሻያ ሥልጠና የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል። በመድረኩ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) በሀገር ደረጃ ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ለውጥ መጥቷል ብለዋል።

በስንዴ ልማት፣ በዲጂታል ግብርና፣ በሜካናይዝድ አመራረት የተገኙ ውጤቶችን ለአብነት አንስተዋል። በዘርፉ ለመጣው ለውጥ ደግሞ የግብርና ቤተሰቡ ጥረት ከፍተኛ እንደኾነ አመላክተዋል። የግብርና ሥራችን ከእጅ ወደ አፍ ሳይኾን እንደ አዋጭ የሥራ መስክ መወሰድ አለበት ያሉት ሚኒስትሩ ይህን ለማሳካትም ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ብሎም ከኮሌጆች ጋር በመተባበር የቀበሌ ግብርና ባለሙያዎች የደረጃ ማሻሻያ ሥልጠና መጀመሩን ገልጸዋል።

ከ7 ሺህ 500 በላይ ሠልጣኞች በመጀመሪያው ዙር በኮምቦልቻ እና ባሌ ተሳታፊ እንደሚኾኑ የገለጹት ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) በቀጣይም በሌሎች ዙሮች ቀሪ ባለሙያዎችን የማሻሻያው ተጠቃሚ እንዲኾኑ ይደረጋል ነው ያሉት። ሥልጠናው ዘመኑ የሚጠይቃቸውን የግብርና አሠራሮች እና ተሞክሮዎች ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊ መኾኑን ጠቅሰዋል።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል የተዘጋጀው የባለሙያዎች የደረጃ ማሻሻያ ሥልጠና ለሀገር ዕድገት መፍትሔ መኾኑን አንስተው ዕድሉን በሚገባ መጠቀም ይገባል ብለዋል። ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ውጤታማ የግብርና ሥራዎችን ተግባራዊ በማድረግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ሚኒስትሯ አመላክተዋል።

ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ስለ እናቶች እንባ ብሎ ሁሉም ወደ ውይይት ይምጣ” በሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ ሴቶች
Next articleየኢትዮጵያ አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ማጠቃለያ መድረክ እየተካሄደ ነው።