“ስለ እናቶች እንባ ብሎ ሁሉም ወደ ውይይት ይምጣ” በሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ ሴቶች

90

ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር ችግር በገጠማት ቁጥር ሴቶች፣ ሕጻናት እና አካል ጉዳተኞች ቀዳሚ ሰለባዎች ናቸው። በአማራ ክልል በተደጋጋሚ በተከሰተው ግጭትም በርካታ ሴቶች በየቦታው ጾታዊ ጥቃት እና ተያያዥ ችግሮችን ማስተናገዳቸው ይታወሳል። በርካታ ሴቶች አልቅሰዋል፣ እናቶች አኹንም ስለልጆቻቸው የጭንቅ ጊዜያትን እያሳለፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያላግባብ ያሉ ጉዳዮች በሙሉ በውይይት ተፈትተው ሰላሟ የተጠበቀች ሀገር እንድትኾን ዓላማ ይዞ ከሰሞኑ በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ላይ ነው። በዚሁ መርሐ ግብር ላይ ያገኘናቸው የሕዝብ ወኪል እናቶች በጭንቀት መኖር በቃን ብለዋል።
ከሰሜን ወሎ የመጡት እናት ጠጂቱ አሊ በአካባቢው የሚገኙ ሴቶች ከሕወሓት ወረራ ወቅት ጀምሮ አስቸጋሪ ጊዜያትን እንዳሳለፉ ገልጸዋል።

ጦርነት ለመላው የሰው ልጆች ፈተና ቢኾንም በተለይም ሴቶች ቀዳሚ ተጠቂዎች ናቸው ብለዋል። ጦርነት ከመሞት በተረፈ ረሀብ እና መጠማትን ይወልዳል፤ ልጇ “ራበኝ” ያላት እናት ደግሞ ጭንቀቷን ቃል አይገልጸውም ሲሉም አብራርተዋል። በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት አጥፍቷል፤ የኑሮ ውድነቱንም አባብሷል ነው ያሉት። እንደ እርሳቸው ገለጻ በየጊዜው መንገድ መዘጋቱ የምርት ዝውውርን ገድቧል፤ እናቶች መሶባቸው ባዶ ኾኖ ለልጅ የሚያጎርሱት አጥተዋል።

“በግጭት ምክንያት የብዙዎችን ሕይወት አጥተናል፤ ሮጠው ያልጨረሱ ወጣቶችን ቀብረናል፤ ከዚህ የባሰ ችግር ከወዴት ይመጣል? ስለዚህ ችግርስ ቁጭ ብሎ መወያያ ጊዜው መቼ ሊኾን ይችላል?” ሲሉም አጠይቀዋል። ችግሮች ሁሉ በምክክር እንዲፈቱ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው፣ ይህንንም በማመን ለሀገራዊ ምክክር ተሳትፎ በባሕር ዳር እንደተገኙም ነግረውናል።

ሌላዋ ከምሥራቅ ጎጃም የመጡት እናትም ሀገራዊ ምክክሩ የችግሮች ሁሉ መቋጫ እንዲኾን ንቁ ተሳትፎ ሊኖረን ይገባል ብለዋል። ምክክሩ እንዳይካሄድ የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ መታዘባቸውን ገልጸው ይህ አካሄድ ትክክል እንዳልኾነም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። መመካከር በየትኛውም መመዘኛ ቢለካ ትክክል እንጅ ስህተት ሊኾን አይችልም ሲሉም ገልጸዋል።

ተመካክረን ሰላም ያለባት እና ለሁሉም የምትመች ሀገር መሥራት አለብን፤ በጦርነት የሚያለቅሱ እናቶችን እንባም ማበስ ግድ ይለናል ነው ያሉት። “እናቱን የሚወድ ሁሉ ስለሴቶች እንባ ብሎ ወደ ጠረጴዛ ውይይት ይምጣ፤ መሳሪያ ይዞ መፎካከር እና መገዳደል ይቁም” ሲሉም የእናትነት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ማንም ይሁን ማን የሚሞተው የሁላችንም ልጅ ነው፤ ለሀገር የክፉ ቀን አለኝታ የኾነ ወጣት ነው እርስ በእርሱ እየተገዳደለ ያለው፤ ይህ በአስቸኳይ እንዲቆም ከልብ የኾነ ውይይት ያስፈልጋል ነው ያሉት። መንግሥትም ለሕዝብ ውይይቶች ኹኔታዎችንን ማመቻቸት፣ የተነሱ የጋራ ሀሳቦችንም ተቀብሎ በመተግበር ለሰላም ቁርጠኛ መኾን አለበት ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅም አጀንዳ መቅረት የለበትም።
Next article“በሀገር ደረጃ ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ለውጥ መጥቷል” ግርማ አመንቴ (ዶ.ር)