
ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል አጀንዳ እያሰባሰበ ነው። ሕዝብ የመረጣቸው ተሳታፊዎችም አጀንዳቸውን እያዋጡ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የዕቅድ ክትትልና ግምገማ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ቡድን መሪ ጌታነህ ማሞ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እጅግ መሠረታዊ በኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲፈጠር የሚሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ የተሰጠውን ኀላፊነት ለመወጣት የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተሳታፊ ልየታ እያደረገ መኾኑንም ነው የተናገሩት። በአማራ ክልል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት አስፈላጊውን ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። አሳታፊነቱን እና አካታችነቱን በጠበቀ መልኩ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ተሳታፊ ሳይኾን እንዳይቀር በጥንቃቄ መሠራቱንም ነው የተናገሩት።
በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የየትኛውም ወገን ሀሳብ ሳይደመጥ እንዳይቀር ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት። በአማራ ክልል የቆዬው ግጭት ሥራዎችን በፍጥነት ለመሥራት ፈታኝ እንደነበር የተናገሩት አሥተባባሪው ችግሮችን በመቋቋም መሥራታቸውንም ገልጸዋል። የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ለሥራቸው ትልቅ አቅም እንደነበር ነው የተናገሩት።
ምክክር ሀገርን ከችግር ያወጣል የሚል ጽኑ እምነት ያላቸው ባለድርሻ አካላት ያደረጉት ድጋፍ የሚደነቅ መኾኑን ገልጸዋል። የማንኛውም አካል አጀንዳ እንዳይቀር ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት። ለኢትዮጵያ አሻጋሪ ሀሳብ ለማምጣት ይሄን አጋጣሚ መጠቀም ይገባል ብለዋል። ሀገር እና ሕዝብን የሚጠቅም፣ የሚያሻግር፣ ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያጸና አጀንዳ መቅረት የለበትም ነው ያሉት።
ተሳታፊዎች ለክልሉም ኾነ ለሀገር የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን እየመረጡ ነው፤ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው የማንም ጣልቃ ገብነት የሌለበት ነው ብለዋል። የአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መርኾዎች ተፈጻሚ እንደሚኾኑም ገልጸዋል።
አካታችነት፣ አሳታፊነት፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት በትኩረት የሚሠራባቸው ናቸው ብለዋል። የትኛውም አካል አልተሳተፍኩም፣ አልተወከልኩም እንዳይል እና እንዲሳተፍ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አጀንዳ አለኝ ካለ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ ማቅረብ እና ማስያዝ እንደሚችልም ተናግረዋል። አጀንዳ አለን የሚሉ ኢትዮጵያውያን አጀንዳቸውን እንዲያቀርቡም ጥሪ አቅርበዋል።
በአማራ ክልል አሉ የሚባሉ አጀንዳዎች ሁሉ እንደሚወጡ ይጠበቃል፤ ያን ማድረግ የሚያስችል ሂደቶችንም አልፈናል ነው ያሉት። ምንም አይነት አጀንዳ ቀረ እንዳይባል የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል ብለዋል። ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ ለማጽናት ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ማሳተፍ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን