በአፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የሚመራ ልዑክ በዓለም አቀፍ የፓርላማ ጉባኤ እየተሳተፈ ነው።

26

ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የሚመራው ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የሚመራው የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የፓርላማ አባላት ልዑክ በ150ኛው ዓለም አቀፍ የፓርላማ ኅብረት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ኡዝቤኪስታን ታሽከንት ገብቷል።

ለ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር አስፈላጊ መኾኑን አሳስበዋል። አፈ ጉባኤ አገኘሁ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ሰላም እና ብልጽግናን ከማረጋገጥ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሰላምን ለማምጣት እንደምትሠራ ገልጸዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አጀንዳ 2063 ጋር የሚጣጣም የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ ነድፋ እየተገበረች እንደኾነም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት የዘላቂ ልማት ግቦችን በማሳካት እና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ እንዲኹም በጤና፣ በትምህርት፣ በንጹህ መጠጥ ውኃ እና በኢነርጂ ተደራሽነት ላይ ጉልህ ለውጥ ማምጣቷን አንስተዋል። የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከልን ጨምሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርን በመተግበር ላይ መኾኗንም አብራርተዋል።

ፓርላማው የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት አስፈላጊ የኾኑ ፖሊሲዎችን እና የሕግ ማዕቀፎችን በመመርመር፣ በማጽደቅ እንዲኹም ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑንም ገልጸዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤቱም ለክልሎች ፍትሐዊ የልማት በጀት ድልድል በማድረግ እና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የመሠረታዊ የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎትን በማስፋፋት እና ጠንካራ የፓርላማ ቁጥጥርን ለማሳደግ ቁርጠኛ መኾኗን መናገራቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየበርሚል ጊዮርጊስ ጸበልን ሀገረ ስብከቱ መከፈቱን እስኪያውጅ ድረስ አማኞች ወደ ቦታው እንዳይሄዱ የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት አሳሰበ፡፡
Next articleለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅም አጀንዳ መቅረት የለበትም።