
ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በቋራ ወረዳ በርሚል ጊዮርጊስ ተብሎ የሚጠራው ሥፍራ የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱ ተገልጿል። የኮሌራ በሽታን መከሰት ተከትሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ለአማኞች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሊቀ አይላፍ አባ ኃይለማርያም ያሳይ ከዚህ በፊት የኮሌራ በሽታ መከሰቱን ምክንያት በማድረግ ወደ አካባቢው የሚመጡ አማኞች በበሽታው እንዳይጎዱ በማሰብ ከምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ እና ከክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመምከር ለአንድ ወር እስከ መጋቢት 19/2017 ዓ.ም መዘጋቱን አውስተዋል፡፡
ሥራ አሥኪያጁ እንዳሉት አማኞች አሁን ወደ ሥፍራው እየመጡ ያሉት ለአንድ ወር በመኾኑ ቀኑን ቆጥረው እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ አመማኞች በሽታው አሁንም በቁጥጥር ሥር ያልዋለ በመኾኑ ወደ በርሚል ጊዮርጊስ ከመምጣት እንዲቆጠቡ ነው ያሳሰቡት፡፡ ቤተክርስቲያኗ አማኞች እንዳይጎዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራች እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡
መንግሥት ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ ቤተክርስቲያኗ ደረጃውን የጠበቀ ለአማኞች የማረፊያ እና የመጸዳጃ ክፍሎችን እና የመጠጥ ውኃ ግንባታ ለማከናወን እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗ የምትሠራው ሥራ እንዳለ ኾኖ ከሚመለከተው የጤና ተቋም ጋር ጠንክራ በመሥራት እና በሽታውን በቁጥጥር ስር በማዋል ለአማኞች ጥሪ ለማድረግ እየሠራች እንደምትገኝ ነው የተናገሩት፡፡
በመልዕክታቸውም አስጎብኝ ማኅበራትም ኾነ የጉዞ ወኪሎች የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ሰዎች ወደ አካባቢው እንዳያመጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ዮሴፍ ጉርባ አካባቢው ላይ ከዚህ በፊትም ምልክቶች ስለነበሩ ማኅበረሰቡ ወደስፍራው እንዳይሄድ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል።
ሰዎች ወደ ሥፍራው እንዲሄዱ የሚቀሰቅሱ አስጎብኝ ድርጅቶች የበሽታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ በጊዜያዊነት ቅስቀሳ እንዲያቆሙም አሳስበዋል። አሁንም ወደ አካባቢው የሚመጡ ሰዎች መኖራቸውን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው በበሽታው የሚያዙ ሰዎች መኖራቸውን ነው የገለጹት። በሽታውን መቆጣጠር እስኪቻል እና ስጋት አለመኾኑ ሲረጋገጥ ወደ ሥፍራው መሄድ እንደሚቻልም ገልጸዋል። እስከዛው ግን ወደሥፍራው ከመንቀሳቀስ መቆጠብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አካባቢው ላይ የኮሌራ በሽታ የሚያስከትለውን ችግር ለመከላከል እና የሰዎችን ጉዳት ለመቀነስ አስፈላጊው ሕክምና እየተደረገ ነው ብለዋል። በሽታው በፍጥነት ወደ ጤነኛ ሰው ተዛምቶ በቀላሉ የሚገድል በመኾኑ ሰዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁም አስገንዝበዋል። ማኅበረሰቡ ስጋት በኾኑ አካባቢዎች ባለመገኘት ራሱን ከኮሌራ በሽታ እንዲጠብቅም አሳስበዋል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን