ዓባይ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ለደንበኞቹ የወለድ ቅናሽ አደረገ፡፡

250

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) የዓባይ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ዘርፈ ብዙ ዓለም አቀፍ ቀውስ የፈጠረውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መቋቋም ያስችላቸው ዘንድ ለደንበኞቹ የወለድ ቅናሽ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የብድሩን የክፍያ ጊዜ፣ ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት እና የባንኩን አቅም ታሳቢ በማድረግ ከ0 ነጥብ 5 እስከ 3 በመቶ ድረስ የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ማድረጉን የዓባይ ባንክ አክስዮን ማኅበር የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት በለጠ ዳኛው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ባንኩ በወረርሽኙ በተለየ ሁኔታ ተጠቂ ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ የሆቴል፣ አስጎብኚ፣ የአበባ ምርት ላኪ እና አቅራቢ የንግድ ዘርፎች ላይ ከፍ ያለ የወለድ ቅናሽ አድርጓል፡፡ ዓባይ ባንክ ይህንን የወለድ ቅናሽ በማድረጉ ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚያጣም ተነግሯል፡፡

በተጠቀሱት ዘርፎቶ ላይ ከግንቦት ጀምሮ በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ ተበዳሪዎች እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸውን የዋና ብድር እና የወለድ ክፍያ ማስተላለፉንም በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

የብድር ማራዘሚያ ጥያቄ ለሚያቀርቡ ደንበኞቹ እንደየሁኔታው እየታየ እንዲፈቀድ ይደረጋልም ተብሏል፡፡ የብድር ማራዘሚያ ጥያቄ በነጻ እንዲሆን እና የቅድሚያ ብድር ክፍያ ቅጣት እንደተነሳም ተገልጿል፡፡ ኤ ቲ ኤም ለሚጠቀሙ ደንበኞቹ የአገልግሎት ክፍያ ነጻ እንዲሆንና ደንበኞቹ በአንድ ጊዜ እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ በኤ ቲ ኤም ማውጣት እንዲችሉ መደረጉንም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

ባንኩ ቫይረሱን ለመከላከል እና በተለያየ ሁኔታ ተጎጂ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተቋቋመዉ ዕርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል፡፡

የዓባይ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ሠራተኞችን ከወረርሽኙ ለመከላከል እየወሰደ ያለውን ርምጃም አቶ በለጠ በመግለጫቸው አብራርተዋል፡፡ “ይህንን አስቸጋሪ ወቅት በኢትዮጵያዊ አንድነት፣ በመተባበር እና በጽናት እንደምንሻገረው ባለ ሙሉ ተስፋ ነን” ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ፡፡

ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ -ከአዲስ አበባ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleአልቃይዳ እና አይ ኤስ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት መግባታቸው ተገለጸ፡፡
Next articleባለፉት ስድስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴው ግድብ 605 ሚሊዮን 523 ሺህ ብር ተሰብስቧል፡፡