የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ የሰብዓዊነት ግዴታችን ነው ።

53

ሰቆጣ: መጋቢት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትዕግስት ፈረደ ድሴምበር 10 ቲጂ ሂውማኒተሪያን ኤድ (December 10 TG HUMANITARIAN AID) የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በሰቆጣ ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ አድርጓል።

ወይዘሮ ላይሽ አበጀ የአካል ጉዳተኛ ናቸው፤ በሰቆጣ ከተማ ከ20 ዓመት በላይ የኖሩ ሲኾን ኑሯቸውንም በቤተ ክርስቲያን ተጠልለው እንደሚኖሩ ነግረውናል። በበጎ አድራጊ ግለሰቦች እጅ የተመሠረተ ሕይዎት እንደሚኖሩ የገለጹት ወይዘሮ ላይሽ አበጀ በወይዘሮ ትዕግስት የተደረገላቸው ድጋፍ የወር ቀለብ እንደሚኾናቸው ገልጸዋል። ስለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉን ያከፋፈሉት የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ በርናባስ ናቸው። የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ የሰብዓዊነት ግዴታችን ነው ብለዋል።

በአሜሪካ የምትኖረው ወይዘሮ ትዕግስት ፈረደ ያደረጉት ድጋፍ መልካም ሥራ እንደኾነ የጠቀሱት ብጹዕነታቸው በቀጣይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ አቅመ ደካሞችን መደገፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዋግ ልማት ማኅበር በመሠረተ ልማቱ ዘርፍ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር መሰል ድጋፎችን በማስተባበር የበኩሉን ኀላፊነት እየተወጣ የሚገኝ ሀገር በቀል ማኅበር መኾኑን የማኅበር ዋና ዳይሬክተር ኃይሌ ወልዴ ተናግረዋል።

ድሴምበር 10 ቲጂ ሂውማኒተሪያን ኤድ ድርጅት መሥራች ወይዘሮ ትዕግስት ፈረደ ከ500 ሺህ ብር በላይ ወጭ በማድረግ 55 ኩንታል ፊኖ ዱቄት ለአቅመ ደካሞች፣ ለእናቶች እና ሕጻናት ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል። ለዚህም በዋግ ልማት ማኅበር ስም አመስግነዋል።

ባለፈው ዓመት በነበረው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ምክንያት በዋግ ኽምራ ባሉ ደጋማ ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ የሚታወስ ነው። በዚኽም ከ242 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወር የሚደርስ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚሹ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምህረት መላኩ ተናግረዋል።

ከዚህም ውስጥ 118 ሺህ ለሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ የተደረገ ሲኾን ቀሪ 124 ሺህ የሚኾኑት ድጋፍ ያላገኙ ወገኖች መኾናቸውን አቶ ምህረት ገልጸዋል።

ወይዘሮ ትዕግስት ፈረደ በመሰረቱት ረጅ ድርጅት አማካኝነት የተገኘው የ55 ኩንታል የዱቄት ድጋፍ ለ275 አቅመ ደካሞች የወር ቀለብ እንደሚኾን የጠቆሙት ኀላፊው ስለተደረገው ድጋፍ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሕዝብ ስም አመስግነዋል።

በቀጣይም መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ለአርሶ አደሮችም የምርጥ ዘር ድጋፍ እንዲቀርብ አቶ ምህረት ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleዜጎችን ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ማሸጋገር መቻሉን የሐረሪ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
Next articleየፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ኮምቦልቻ ከተማ ገቡ።