ዜጎችን ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ማሸጋገር መቻሉን የሐረሪ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

58

አዲስ አበባ: መጋቢት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶአደር ከዲር አልዋል እና አብዲ በኸር በሐረሪ ክልል ኤረር ወረዳ ዶዳታ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።

የኤረር ወንዝን በመጥለፍ እና የከርሰ ምድር ውኃን በመጠቀም የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ሲያለሙ ነው ያገኘናቸው።

ከአሁን በፊት የመስኖ ልማት ግንዛቤ ባለማግኘታቸው ማሳቸው ጾሙን ሲያድር እንደነበር ነው አርሶ አደሮቹ ያስታወሱት።

በዚህም ለረጅም ጊዜ ሕይወታቸውን በተረጅነት እና በጠባቂነት ሲገፉ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ይኹን እንጅ አሁን ላይ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ለዘመናት ጾሙን ሲያድር በነበረው ማሳቸው ላይ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ፓፓያ፣ ሙዝ እና ሌሎች አትክልቶችን በስፋት በማልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መኾናቸውን ነግረውናል።

በመንግሥት በኩል ከሙያዊ ድጋፍ እና ክትትል በተጨማሪ የሞተር እና የምርጥ ዘር አቅርቦት እያገኙ መኾኑን አርሶአደሮቹ ገልጸዋል።

የሐረሪ ክልል ለመስኖ ልማት የሚኾን ለም አፈር እና ምቹ የአየር ንብረት እንዳለው የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ነስረዲን አሕመድ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ ከ4ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ እየለማ መኾኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ ከ12ሺህ በላይ አርሶአደሮች በበጋ መስኖ እየተሳተፉ ነው ብለዋል።

በኢረር ወረዳ ብቻ በሴፍትኔት ይተዳደሩ የነበሩ 800 አባወራዎችን በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል።

በኤረር ወረዳ በሴፍትኔት የሚተዳደሩ 800 ነዋሪዎችን በ2018 ዓ.ም በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ እና ከተረጅነት ሙሉ በሙሉ ለማውጣት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ነው የጠቆሙት።

የበጋ መስኖ በክልሉ ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን አቶ ነስረዲን ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡን ከተረጅነት ከማውጣት ባሻገር የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድም ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

እንደ ቢሮ ኀላፊው ገለጻ 120 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ሽንኩርት አሁን ላይ በ30 ብር እየተሸጠ ነው።

80 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ቲማቲም አሁን ላይ 40 ብር እየተሸጠ ነው ብለዋል።

10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ የግብርና ግብዓቶች ለአርሶአደሮች ተደራሽ መደረጉንም ምክትል ኀላፊው ጠቁመዋል።

ለአልሚ አርሶአደሮችም 850 ኩንታል የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርጥ ዘር እንዲኹም 1ሺህ 200 የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

52 የሞተር ፓንፖች በመንግሥት በኩል ለአርሶአደሮች የተሠራጨ ሲኾን አርሶአደሮች ከሞተር ፓንፕ በተጨማሪ የሶላር ፓምፕን ተጠቅመው እንዲያለሙ እየተሠራ ነው ተብሏል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ-ከሐረር

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየከተማዋን ንግድ እና ኢንቨስትመንት ለማሻሻል እየተሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
Next articleየተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ የሰብዓዊነት ግዴታችን ነው ።