የከተማዋን ንግድ እና ኢንቨስትመንት ለማሻሻል እየተሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

28

ጎንደር: መጋቢት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ የንግድ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሻሻል ያለመ አጋር አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን የተናገሩት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው አሁናዊ የንግድ ሂደቱን መመርመር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

መድረኩ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማመላከት ያለመ መኾኑንም ገልጸዋል።

የከተማዋ የግብር አሠባሠብ ሂደት ውስንነት ያለበት መኾኑ ተገልጿል። ግብር እና የከተማ ልማት ተያያዥ መኾናቸውን በመገንዘብ የከተማዋን የግብር አሠባሠብ ሂደት የማዘመን ሥራን በወቅቱ መከወን ይገባል ብለዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቴዎድሮስ ጸጋየ ጎንደር ከተማ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ካላቸው ከተሞች ተርታ የምትመደብ መኾኗን ገልጸዋል።

በከተማዋ ከ15 ሺህ በላይ ነጋዴዎች መኖራቸውን ያሳወቁት አቶ ቴዎድሮስ በ2017 ዓ.ም 2 ሺህ 970 አዲስ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓቱ መግባታቸውን ተናግረዋል።

የተፈጠረው የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት ለንግድ እንቅስቃሴው መቀዛቀዝ ትልቁን ድርሻ ይወስዳልም ብለዋል።

ሕጋዊ እና የተሳለጠ ግብይት በመፍጠር የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግም ምቹ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት፣ የተጀመሩ ኢንቨስትመንቶች ወደ ምርት እንዲገቡ በማድረግ ብሎም ሕገወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች የጸጥታው ችግር የንግዱን እንቅስቃሴ መፈተኑን ጠቁመው የከተማዋን የንግድ ሥራ ወደ ቀደመው ለመመለስ ባለድርሻ አካላት እና የንግዱ ማኅበረሰብ በጋራ መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።

በውይይቱ ባለድርሻ አካላት፣ ነጋዴዎች፣ ጫኝ እና አውራጅ እንዲሁም ደላሎች ተሳታፊ ኾነዋል

ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ187 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እየተሠራ ነው።
Next articleዜጎችን ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ማሸጋገር መቻሉን የሐረሪ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።