ከ187 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እየተሠራ ነው።

22

ደሴ: መጋቢት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2017/2018 የምርት ዘመን ከ187 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በክልሉ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር እንደሚሸፈን የገለጸ ሲኾን ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር የሚኾነው በዋና ዋና ሰብሎች በኩታ ገጠም እንደሚሸፈን ተመላክቷል።

የምርት ዕቅዱን ለማሳካት የአፈር ለምነትን በሚጨምሩ አሠራሮች፣ በሰብል ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲሁም የባለሙያዎችን እና የአርሶ አደሮችን ግንኙነት በሚያሳድጉ ሥልጠናዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና ለግብርና ባለሙያዎች እና ኀላፊዎች እየተሰጠ ይገኛል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው የምርት ዕቅዱን ለማሳካት የግብዓት አጠቃቀምን ጥራት ማሳደግ፣ በስፋት ከሚመረቱ ሰብሎች ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ፣ የአፈርን አሲዳማነት መከላከል እና ማከም እንዲሁም የተሻሻሉ አሠራሮችን በመጠቀም በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የግብርናውን ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ከምርምር ተቋማት፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ምክትል ቢሮ ኀላፊው አስረድተዋል።

የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሥልጠናው በአካባቢያቸው ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ አቅም እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

በቀጣይም ላልሠለጠኑ የግብርና ባለሙያዎች አቅማቸውን በማሳደግ በምርት ዘመኑ የታቀደውን ለማሳካት ከቅድመ ዝግጅት እስከ ትግበራ በቅንጅት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በአምስት ማዕከላት የአቅም ግንባታ ሥልጠናው ለግብርና ባለሙያዎች እና ኀላፊዎች እየተሰጠም ይገኛል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ስለ ሀገር ይመክራሉ፣ ስለ ሕዝብ ይዘክራሉ”
Next articleየከተማዋን ንግድ እና ኢንቨስትመንት ለማሻሻል እየተሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።