“ስለ ሀገር ይመክራሉ፣ ስለ ሕዝብ ይዘክራሉ”

37

ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ ኢትዮጵያ እየተመከረ፣ ስለ ሕዝብ እየተዘከረ ነው። የመከረች ሀገር አንድነቷን ታጸናለች። የመከረች ሀገር ሰላሟን ትጠብቃለች። የመከረች ሀገር ሕዝቦን ከፍ ከፍ ታደርጋለች።

ብልሆች ስለ ሀገር እየመከሩ፣ ስለ ሕዝብ እየዘከሩ ነው። የደመቀውን ታሪክ በምክክር ይጽፉ ዘንድ በአንድነት ተሠባሥበዋል። በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ለሀገራቸው መላ እየዘየዱ ነው።

በግጭት እልፍ ጉዳይ እና በጦርነት ብዙውን አጥተዋልና ከሁሉም የተሻለውን ምክክርን አስቀድመዋል። ለምክክሩ የተገባውን ነገር ለማድረግ ተሠባሥበዋል።

በአማራ ክልል መጋቢት 27/2017 ዓ.ም የተጀመረው የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ ዛሬም ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ በምክክር ትጸናለች። ሀገር በምክክር ከፍ ትላለች። ችግሮች ሁሉ በምክክር ይፈታሉ ብለው ያመኑ ተሳታፊዎች አጀንዳዎች ላይ እየተወያዩ ነው።

ሀገር የምትድንበትን፣ ሰላም የሚጸናበትን፣ ፍትሐዊነት የሚረጋገጥበትን፣ አንድነት የሚደረጅበትን ሀሳብ እያዋጡ ነው።

ለቀናት በሚዘልቀው የአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደት ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተሳታፊዎች ለዘመናት የነበሩ ጥያቄዎችን ለመፍታት ምክክር ቀዳሚውም፣ ተከታዩም፣ የመጨረሻው እና ብቸኛውም ምርጫ ነው ብለዋል።

በአጀንዳ ማሠባሠቡ እየተሳተፉ ያሉ ወገኖች የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በምክክር ነው ይላሉ።

የምክክር ሂደቱ ለኢትዮጵያ ተስፋ ነው ብለዋል።

በአጀንዳ ማሠባሠቡ እየተሳተፉ ያሉ ወገኖች ለኢትዮጵያ የሚበጀውን እያደረግን ነው ይላሉ።

ምክክር የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ያልተገኙ ዕድሎችን የሰጠ፣ የዘመናት ጥያቄዎችን የሚፈታ መኾኑንም አንስተዋል።

በአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደቱም ሀሳባቸውን በነጻነት እና በግልጽነት እያነሱ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ሁሉም ወገኖች በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሳምንቱ በታሪክ
Next articleከ187 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እየተሠራ ነው።