የአቶ አደም ፋራህ መልዕክት፦

85

ባሕር ዳር: መጋቢት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት እንደ መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ የአገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ለማስተግበር በከፍተኛ ቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን።

የሪፎርሙ ዓላማ በከፍተኛ ትጋት፣ ቁርጠኝነት እና ፍጥነት ይሳካ ዘንድ የመንግሥት ከፍተኛ መሪዎች ተሳታፊ የኾኑበት መድረክ በአፍሪካ ሊደርሺፕ አካዳሚ “ልህቀት በሰው ተኮር አገልግሎት” በሚል መሪ ሃሳብ የአቅም ግንባታ መድረክ እያካሄድን ሲኾን በመድረኩም ገንቢ ሃሳቦች እየተገኙበት ነው።

ሪፎርሙ አምስት ዋና ዋና መነሻ ጉዳዮች ያሉት እና እነዚህንም ትኩረት በማድረግ ተገልጋዩን የኅብረተሰብ ክፍል በከፍተኛ ኹኔታ ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ መሪውም ኾነ ፈጻሚ አካሉን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሲኾን በጥልቅ ምክክር እየዳበረ እና እየበለጸገ የሚሄድ የትግበራ ሂደትን ያነገበ ነው።

በመነሻነት ከተወሰዱ ጉዳዮች በቀደምትነት የሚጠቀሰው የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድን እና የሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራን በስኬት ለመፈጸም የሚያስችል መኾኑ ተጠቃሽ ነው።

የመንግሥትን የመፈጸም አቅም በመገንባት ቀልጣፋ፣ አስተማማኝ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት አሰጣጥን ለመተግበር በር ከፋችም ነው።

እንዲሁም ሂደቱ የመደመር እሳቤን እና ፕራግማቲክ አቅጣጫን መሰረት ያደረገ እሳቤን ያገናዘበም ነው። ይህም በመኾኑ ነባር የኾኑ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል፤ ስህተቶችን እያረቀ የሚሄድ ብሎም በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ጥንካሬዎችን ደምሮ ለመጠቀም የሚያስችል መርህን የሚከተል መኾኑ የትግበራውን ትሩፋት አጓጊ አድርጎታል።

ከዚህም ባሻገር ሰው ተኮር እሳቤን መሰረት ያደረገ እና በሲቪል ሰርቪሱ ዙሪያ ያሉ አካላትን በተለይም ተገልጋዩን፣ ሰራተኛውን እና መሪውን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል እንቅስቃሴ ተደርጎም የተቀረጸ ነው። ሂደቱም ግልጽነት፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ ፈጠራ እና ፍጥነትን ለማሳደግ፣ የተገልጋዩን ጥቅም የሚያስከብር የትግበራ አንጓዎች ያሉት ነው።

በተጨማሪም ሪፎርሙ ከሕገ መንግሥቱ እና ከፌደራል ሥርዓቱ ጋር የተጣጣመ ነው። የአንድነታችን መገለጫ የኾኑ እሴቶችን በተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ የሚያደርግ አላስፈላጊ የኾኑ የኢ-ፍትሐዊነት ቅርፊቶችን የሚገፍ፣ በፌደራል እና በክልል መንግሥታት የጋራ ጥረት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበታል።

በጥቅሉ ጠንካራ እና ቅቡልነት ያላቸው ተቋማትን ለመገንባት እድል የሚሰጥ በመኾኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለግቦቹ መሳካት እና ለትግበራ ሂደቱ መሳለጥ ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡ በዚህ አጋጣሚ አደራ ለማለት እወዳለሁ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሹዋሊድ በዓል አብሮነትን እና ወንድማማችነትን ለማጠናከር የሚያስችል በዓል መኾኑን የሐረሪ ክልል አስታወቀ።
Next articleየፌደራል መሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የእግር ኳስ ጨዋታ አካሄዱ።